መንግስት የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል -ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል -ተሳታፊዎች
ቡታጅራ ፤ ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ)፡- መንግስት የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር በገጠርም ሆነ በከተማ እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የቡታጅራ ከተማ የህዝባዊ ውይይት መድረክ ተሳታፊዎች ገለፁ፡፡
በከተማው "የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ መንግስት የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ በማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
የውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አቶ ወንደወሰን ኃይሌ አብሮነትን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመንግሥት በተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በዚህም በምስራቅ ጉራጌ ዞንና በማረቆ ልዩ ወረዳ መካከል ለረጅም ዘመናት ተከስቶ የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፍታት በመቻሉ በተጨባጭ የሚታይ ውጤት የተመዘገበበት ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
በቡታጅራ ከተማም ይሁን በአካባቢው የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠልና ሰላማችንን በማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን በመሆን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ከድጃ ሻፊ በበኩላቸው መንግሥት በአካባቢው ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በምግብ ራስን በመቻል ከተረጂነት ለመውጣት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በቡታጅራ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎች የመጪውን ትውልድ ከግንዛቤ ያስገባ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስራ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ክፍሉ ታምራት ናቸው፡፡
መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አምራቹንና ሸማቹን ህብረተሰብ በቀጥታ በማገናኘት እያከናወነ ያለውንን ተግባር ሊያጠናክር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ እንዳሉት ክልሉ ያለውን የመልማት አቅም በመጠቀም ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ቅንጅታዊ ጉዞን ማጠናከር ይገባል፡፡
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እራስን ለመቻል የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ለማገዝ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትግበራ ላይ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ መንገድ የሚከሰትን የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ማህበረሰቡ በአካባቢው ያለውን ፀጋ አልምቶ በመጠቀም ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት የሚጠበቅበትን ግዴታ መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው የዞኑ አስተዳደር በቀጠናው ዘላቂ ሰላምን ከማስጠበቅ አንስቶ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በምስራቅ መስቃንና በማረቆ ልዩ ወረዳ የነበረውን የሰላም ችግርን በቅንጅት በመፍታት ማህበረሰቡን በልማት እንዲተሳሰር ስለመደረጉና የጋራ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራ ስለመጀመሩም ተናግረዋል፡፡
በከተማው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት የሚያስችሉ ከሰንበት እስከ የሰንበት የገበያ ማዕከላትን በማደራጀት ወደ ትግበራ መገባቱን የተናገሩት የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱ አህመድ ናቸው፡፡
በዚህም ምርት በተመጣጣኝ እንዲቀርብ እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቅሰው በተለያየ መንገድ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ማህበረሰቡን ለምሬት የሚዳርጉ አካላትን የመቆጣጠር ስራ እንደሚጠናከርም ገልፀዋል፡፡