ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በተለያዩ አካባቢዎች የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከየካቲት 16/2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ ምዕራፍ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደቱ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ብለዋል።
በዚህም በአስራ አንድ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን የመለየትና አጀንዳ የማሰባሰብ ስኬታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም የህብረተሰቡን ፍላጎት በማካተት በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማደራጀትና ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ግልጸኝነት፣ አካታችና ገለልተኝነት ለማስጠበቅም ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ሲቪል ማኅበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግልጸኝነትና አካታችነት ምኅዳር ለማስጠበቅም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር አጀንዳ ማሰባሰብና ተወካዮችን ማስመረጥ ያስቻለ ስኬታማ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
በውጭ የሚኖሩ ዜጎች አጀንዳቸውን በማስረከብ ተወካዮቻቸውን የማስመረጥ ሥራም ተሰርቷል ብለዋል።
በትግራይ ክልልም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን ጋር በሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥልቅ ውይይቶች መካሄዳቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማወያየት አጀንዳ የማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማካሄድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በማለም እየሰራ ይገኛል።