ቀጥታ፡

የኢትዮ-ሕንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብር የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያፋጥን የደቡብ ደቡብ ትብብር ወሳኝ መገለጫ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ሕንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብር የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያፋጥን የ"ደቡብ-ደቡብ ትብብር" ወሳኝ መገለጫ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያና ሕንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምርና ትምህርትን ትብብር ለማሳደግ ያለመ መርሃ ግብር ይፋ ሆኗል።


 

መርሃ-ግብሩም በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና በሕንድ ስመ-ጥር የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ትብብር በአምስት ዓመታት ውስጥ 1ሺ 200 የድህረ-ምረቃ(ፒኤችዲ) ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎችን ለማሰልጠን ዓላማ አድርጓል።

በመርሃ-ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ፤ ኢትዮጵያና ሕንድ መካከል ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።

የኢትዮ-ሕንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትብብር መርሃ ግብርም በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃብት በመፍጠር የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በትብብር መርሃ ግብሩ የተካተቱ ስምንት የሕንድ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶችም ችግር ፈቺ የምርምርና ፈጠራ ሥራዎችን በማካሄድ የደቡብ ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝትም የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማሸጋገር እንዳስቻለ አስረድተዋል።


 

የኢትዮ-ሕንድ የጋራ የድህረ-ምረቃ ትምህርት አስተባባሪ ፕሮፌሰር ክሪሽና ራጅ፤ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውህሎትና በቴክኖሎጂ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ነው ብለዋል።

በኢትጵያና ሕንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የተፈጠረው የትብብር አጋርነትም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እንደሚጫዎት ገልጸዋል።

ኢትዮ-ሕንድ የትምህርት የትብብር መርሃ-ግብር ማስጀመሪያ የተገኙት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታደሰ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ መርሃ ግብሩ የሀገራቱን የትምህርት ትብብር ዘላቂ አጋርነትን ያረጋግጣል ብለዋል።

የኢትዮ-ሕንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብር የሰው ሃብት ልማት አቅምን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) ናቸው።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሀገራቱ የምርምርና ትምህርት ተቋማት ትብብር የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን የምርምር ውጤት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያሳድጋል ብለዋል።

መርሃ-ግብሩ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት የሚመጥን ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት በምታደርገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም