ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስጠበቀና የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ትብብርን ያጎለበተ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ያስጠበቀና የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ያጎለበተ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኑነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንትን እያሳለጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር፣ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት፣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትና ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች መገዛት የሚሉት አንድ ሀገር በውጭ ግንኙነት የሚከተላቸው ዋና ዋና መርሆች ናቸው።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትም ከትናንት እስከዛሬ ከራስ ብሔራዊ ጥቅም የሚቀዳ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተመሰረተ የኢኮኖሚና ቅድሚያ ለጎረቤት ዲፕሎማሲያዊ ትብብርን እያጎለበተ ይገኛል።

ይህም የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ገናና የሥልጣኔ ታሪክ ከአሁናዊ ዓለም ጋር በማሰናሰል ከብሔራዊ ክብርና ፍላጎት የተወዳጀ ፍሬያማ የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን በማጎልበት ወርቃማ ዕድል ሆኖ እያገለገለ ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዜጎችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ተደማጭነትና ልዕልና ለማስከበር አዎንታዊ ተፅዕኖ አላቸው ብለዋል።  

የመደመር እሳቤም የዜጎችን አንድነት በማስጠበቅ የኢትያጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ክብር  ያስጠበቀና የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ያጎለበተ መሆኑን ገልጸዋል።

የመደመር መንግስት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሉት ወሳኝ መርሆች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም የውጭ ኢንቨስትመንትና የንግድ ትብብርን በማሳደግ የጋራ ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ የትብብር መርህ መሰረት መሆኑን የአውሮፓ ሕብረትን በአብነት ጠቅሰዋል።


 

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስልጠና ክፍል ዳይሬክተር ጀነራል መላኩ ሙሉዓለም፤ ኢትዮጵያ በትብብርና አብሮ ማደግ ላይ የተመሰረተና በረጅም ታሪክ የዳበረ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS+) አባልነትን መቀላቀሏም የአፍሪካን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማንጸባረቅ የሚረዳ ወሳኝ የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በሰጥቶ መቀበል መርህ የዳበረውን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ለማሳደግ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም