ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ከመገንባት ባለፈ ለብዝሃ ሕይወት መጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እያከናወነች ያለው ተግባር በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ከመገንባት ባለፈ ለብዝሃ ሕይወት መጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በስፋት የሚተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነትና መሪነት የተጀመረ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።

ይህ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመመከት፣ የአገሪቷን የደን ሽፋን ለማሳደግና በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሰረተ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች እንዲተከሉ በማድረግ ረገድ ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፈ ስኬታማ ተግባር ተመዝግቧል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ (ዶ/ር) እንዳሉት ፤ የአየር ንብረት ለውጥ በብዝሃ ሕይወት ህልውና ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ለሥነ-ምህዳር መመሰቃቀልና ለዝርያዎች መጥፋት ዋነኛ መንስኤ እየሆነ ይገኛል።

ይህንን ስጋት ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥን ለመመከት የሚከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እያከናወነች ያለው የችግኝ ተከላ ተግባር፣ ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት እውን ለማድረግ መሠረት እየጣለ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

እንደ ካርታ ካስኬ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ የምግብ ሥርዓት ከግብርና ምርታማነትና ከብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ፣ ኢንስቲትዩቱ ይህንን ሥርዓት ለማጠናከር የተለያዩ የአሰራር ስልቶችን ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ለአብነትም የማህበራዊ ዘር ባንኮች ጥምረት አንዱ ሲሆን፤ ይህም በየአካባቢው ያሉና የማይበገር የምግብ ሥርዓትን እውን ማድረግ የሚያስችሉ የሰብል ዝርያዎችን መጠበቅ ያስችላል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለአካባቢ ጥበቃና ደህንነት መረጋገጥ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም የብዝሃ ሕይወት ሀብትን በአግባቡ ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እያገዘው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም