ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክሩን እድል ልንጠቀምበት ይገባል-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክሩን እድል ልንጠቀምበት ይገባል-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ሀዋሳ፤ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ) ፡-የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክሩን እድል ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታችና አሳታፊ የሆነ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ይቻል ዘንድ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
በእስካሁኑ ሂደትም የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን በማገባደድ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለመሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የምክክር ሂደቱንና አጠቃላይ የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ኢዜአ በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራርና አባላትን አነጋግሯል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ በለጠ ሲጌቦ፤ በዓለም ላይ የተለያዩ ሀገራት በምክክር ከመበተን ወደ አንድነት በመምጣት ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ መቻላቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ያለው ምክክር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ከግጭት ለመውጣት ከምክክር የተሻለ እድልና አማራጭ የለም ሲሉም ተናግረዋል።
የምክክር ሂደቱ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በመሆኑ በአጀንዳ ላይ ተመካክሮ በመግባባት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታትና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሁላችንም ግዴታ ነው ሲሉ አንስተዋል።
እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አጀንዳችንን ለኮሚሽኑ ማቅረብ ችለናል ያሉት አቶ በለጠ፥ በምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ለስኬታማነቱ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ዋና ሊቀመንበርና የጋራ ምክር ቤቱ አባል አቶ ለገሰ ላንቃሞ፤ የምክክር ሂደት የግጭትና ጦርነት ምክንያቶችን በመግባባት መቋጨት የሚያስችል ቁልፍ መፍትሄ በመሆኑ በትኩረት እየተሳተፍን እንገኛለን ብለዋል።
ከመነሻው ጀምሮ በተሳታፊ ልየታም ሆነ በአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች ላይ የፓርቲያቸው ተሳትፎ መኖሩን አንስተው፥ ለምክክሩ ሂደት ውጤታማነት እስከመጨረሻው እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ኤርሚያስ፥ የፖለቲካ ስብራቶችን በማከም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፅኑ መሠረት እንዲኖረው መንግስት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በመፍታት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር መመካከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ከምክክር ውጭ የሚደረግ የሃይልና የጥፋት እንቅስቃሴ አንዳችም መፍትሄ የማያመጣ በመሆኑ ይህንን እድል ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መመካከር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፥ በአጀንዳዎቻችን ላይ በመምከር ለሀገርና ለትውልድ የሚበጅ ታሪክ እንስራ ሲሉ ተናግረዋል።