የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የተሟላ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የተሟላ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው
ወልቂጤ፤ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መያዛችን የተሟላ፤ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው ሲሉ የወልቂጤ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የዲጂታል ኢትዮጵያን እቅድ ለማሳካት እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ አገልግሎትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም መሰረት የፋይዳ መታወቂያን በመያዝ ዜጎች የሚፈልጉትን መንግስታዊና ማህበራዊ አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወልቂጤ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መያዛችን የተሟላ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ በላይነሽ ገብሬ፤ የፋይዳ መታወቂያ በተደራጀ መልኩ የተፋጠነ አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የመታወቂያውን አስፈላጊነት በመረዳትም ከራሳቸው ባለፈ ከ5 ኣመት በላይ የሆኑ ልጆቻቸው የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ እንዲያወጡ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ መልስ ዶርጌ፤ የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ለአገልጋይም ሆነ ለተገልጋይ የተፋጠነ እና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚኖሩት ወጣት ጥላሁን ሸዋረጋ እና ወጣት ታገሱ ደጉ፤ የፋይዳ መታወቂያ በመያዛቸው በተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቀላጠፈ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ እና የፋይዳ ብሄራዊ መታወቂያ አገልግሎት ግብረ ሃይል አስተባባሪ ዳርጌ ተክሉ፤ በዞኑ እስካሁን በ58 ማእከላት 249 ሺህ 951 ዜጎች የፋይዳ ድጅታል መታወቂያ ተመዝግበው መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት አመትም 732 ሺህ 600 ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለዜጎች ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እያስቻለ መሆኑን አንስተው፥ ሌሎችም መታወቂያውን በመያዝ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መክረዋል።