በክልሉ የሰፈነው ሰላም ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትና ለጎብኚዎች ቁጥር ማደግ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሰፈነው ሰላም ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትና ለጎብኚዎች ቁጥር ማደግ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው
ጎንደር፤ታሕሳስ 11/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የሰፈነው ሠላም ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትና ለጎብኚዎች ቁጥር ማደግ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ።
የጎንደር ከተማና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባውን የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ከጎብኚዎቹ ውስጥ ቀሲስ አደራጀው አዳነ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና በመጠበቅ ያከናወናቸው ተግባራት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ አስቻይ ሁኔታ የፈጠረ ነው ብለዋል።
መንግስት በችግር ውስጥም ሆኖ ያከናወናቸው የቱሪዝም ልማት ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸው፤ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ጎርጎራ መንፈስን የሚያድስ ድንቅ የተፈጥሮ በረከትና ጸጋ የተሰጠው ስፍራ ነው ያሉት ወይዘሮ ሰአዳ አሊ ናቸው።
ተፈጥሮ የለገሰችንን የቱሪዝም ሀብት አልምቶ ለመጠቀም ሰላም ወሳኝና ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አለመሆኑን ጠቁመው፥ ሰላም እንዲጸና አጥብቀው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አቶ ብርሀኑ በለጠ በበኩላቸው፥ታሪክን ባሕልንና እምነትን ባዛመደ መልኩ ዘመናዊነትን ተላብሶ የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት አካባቢው ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው ብለዋል።
ቱሪዝም ሀገር ይገነባል የዜጎችንም ህይወት ይቀይራል ያሉት አቶ ብርሀኑ፤ የጎርጎራ ፕሮጀክት መንግስት ለዘርፉ ልማት የሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ፤ ክልሉ የቱሪዝም ሀብቶችና ጸጋዎችን በመለየትና አልምቶ በመጠቀም ረገድ ሰፋፊ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
ቱሪዝም በባሕሪው ሰላም ይፈልጋል ያሉት ሀላፊው፥ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሰፈነው ሰላም ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትና ለጎብኚዎች ቁጥር ማደግ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የሰፈነውን ሰላም ዘላቂነቱን በማረጋገጥ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማሳደግ እንዲቻል ሕብረተሰቡ የሰላም ግንባታ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በጉብኝቱ ላይ አመራሮች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶች ወጣቶችና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።