ቀጥታ፡

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል-ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ

ጅግጅጋ፤ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ)፦የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት የተቀናጀ ጥረት የሚደረግ መሆኑን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ገለጹ።

በሶማሌ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተጀመረ ሲሆን በማስጀመሪያ መርሐግብር ላይ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ እና ሌሎች የፌዴራል የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ዛሬ አገልግሎት የጀመረው የጅግጅጋ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን እንግልት በማስቀረት ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል በመሆኑ ተጠያቂነትን ለማስፈንም እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ማዕከሉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ዘመናዊ መሰረተ ልማት እና የሰው ሀይል የተሟላለት መሆኑንም አንስዋል።

አገልግሎቱን ለማስፋፋትም በቀጣይ በክልሉ 13 ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።


 

በመሆኑም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሌሎች ከተሞችም በማስፋት የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት የተቀናጀ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፥ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ፣ ከአድሎ የጸዳ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ መንግሥትና ህዝብን የበለጠ የሚያቀራርብ እንዲሁም ሰው ተኮር የአገልግሎት ልህቀትን ለማረጋገጥም የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ማዕከሉ መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የጀመረው ሪፎርም ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም አብራርተዋል።

ዛሬ አገልግሎት የጀመረው ማዕከሉ 9 ተቋማትን በውስጡ የያዘ ሲሆን 32 አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም