ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ የማሕበረሰብ አገልግሎትን እያጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ የማሕበረሰብ አገልግሎትን እያጠናከረ ነው
ወልዲያ ፤ ታሕሳስ 11/2017(ኢዜአ)፡- ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የማሕበረሰብ አገልግሎትን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ ።
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አማረ ቢሆን (ዶ/ር )፤ ዩኒቨርስቲው አገልግሎቱን የሚሰጠው በወልዲያ፣ በሰሜን ወሎና በዋግ ኸምራ አካባቢዎች ነው።
በዚህም ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ በግብርና፣ በጤና፣ በትምሕርት፣ በከተሞች ዲዛይን ንድፍና በቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይ በማተኮር የማሕበረሰብ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በጤናው ዘርፍ 78 የዩኒቨርሲቲውን ባለሙያዎች በመመደብ በወልዲያ ስፔሻላይዝድ ጠቅላላ ሆስፒታል በቀዶ ሕክምና ላይ በነጻ እያገለገሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የወልዲያ ከተማን የወንዝ ዳር ልማትን ዘመናዊና ሳቢ ለማድረግ የዲዛይንና የከተማ አገልግሎቱን አሰራር በቴክኖሎጂ በማስደገፍ እንዲሰራ እገዛ ተደርጓል ብለዋል።
በትምሕርት ዘርፉም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በቁሳቁስና በስልጠና በማገዝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባከናወነው የማሕበረሰብ አገልግሎት ስራም ከ101 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አውስተው፤ ተቋሙ የማሕበረሰብ አገልግሎቱ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎችን በመመደብ የነበረባቸውን የስራ ጫናና የመደራረብ ችግር በመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ያሉት ደግሞ የወልዲያ ስፔሻላይዝድ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ የኋላው ናቸው።
ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የነበሩ የቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ወገኖችን በዩኒቨርሲቲው እገዛ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ቀጥሎ እንዳለም አንስተዋል።
በሐብሩ ወረዳ የቁጥር 28 ቀበሌ ነዋሪ አቶ አሕመድ ሐሰን በሰጡት አስተያየት ፤ በፍየል እርባታ ስራ ብዙ ቢደክሙም የሚያገኙት ጥቅም አነስተኛ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዩኒቨርሲቲው ባለሙያ እገዛ የተደረገላቸው የፍየል ዝርያ ማሻሻያ በአካል የገዘፉና የስጋ ምርታቸው ከፍተኛ የሆኑ በማርባት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።