ቀጥታ፡

በሎጅስቲክስ ዘርፍ በተከናወኑ ስራዎች ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች በዘርፉ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ለጉምሩክ ኮሚሽን "ለኤሌክትሮኒክ ካርጎ" አገልግሎት የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።


 

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የቁሳቁስ ርክክቡን ባከናወኑበት ወቅት እንደገለጹት፤ አዲሱ የቴክኖሎጂ ድጋፍ የገቢና ወጪ ንግድ ዕቃዎችን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ፣ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነው።


 

ቴክኖሎጂው ዕቃዎችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ በማሸግ ካሉበት ተነስተው መዳረሻቸው እስኪደርሱ ድረስ ያለምንም መቆራረጥና መቆም እንዲጓጓዙ ያስችላል።

ይህ አሰራር በተለይ በመንገድ ላይ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የዕቃ ቅሸባዎችንና ባዕድ ነገር የመቀላቀል አደጋዎችን በዘላቂነት ይከላከላል ብለዋል።

ሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ሕጋዊ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረጉ ጥረቶችንም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚገታ ገልፀው፥ አሰራሩ የሎጅስቲክስ ዘርፉን አጠቃላይ አፈጻጸም በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚያስችል አስታውቀዋል።

በሎጅስቲክስ ዘርፍ ለታየው መሻሻል የጉምሩክ ኮሚሽን የአንበሳውን ድርሻ መወጣቱን ገልፀው፤ በቀጣይም በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ለማላቅ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ለ10 ዓመታት ተዘጋጅቶ የነበረው የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ መከለሱን አስታውቀዋል።


 

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ የተከለሰ ስትራቴጂ፣ በ"መደመር" እይታ ወደ ኋላ የቀሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን የሥራ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ናቸው።


 

ድጋፉ ደህንነቱ የተጠበቀና የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር በማስቻል ለኮሚሽኑ ትልቅ እገዛ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም