በሀዲያ ዞን ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዲያ ዞን ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ
ሆሳዕና ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፡-በሀዲያ ዞን ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ አስተዳደር ገለፀ፡፡
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዮስ አኒዮ እንደገለፁት ሰሞኑን "የጉባ ብስራቶት፣ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የህዝብ ውይይት መድረክ በዞኑ ህዝብን በማስተባበር የልማት አቅሞችን ወደ ውጤት ለመቀየር የሚደረጉ ጥረቶች አበረታች መሆናቸው የተገለጸበት ነው፡፡
በዚህም የሚታዩ መነቃቃቶችን በማስፋት መስራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የዞኑ አስተዳደር በአካባቢው ያለውን ፀጋና ሀብት በመጠቀም የህብረተሰቡን ኑሮ በማሻሻል ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መስራቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በሆሳዕና ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ፣ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተከናወነ ያለው ተግባር መጠናከር እንዳለበት በውይይቱ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡
ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራን የሚያሰፉ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ከተወያዮች መነሳቱን ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡
እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጉዳይ በውይይት መድረኩ ከተነሱ ጉዳዮች ይጠቀሳል ብለዋል።
የዞኑ አስተዳደርም በውይይት መድረኩ የተነሱ የልማት ጥያቄዎችን ጨምሮ ሌሎችንም የአካባቢውን ፀጋና የማህበረሰቡን አቅም አስተባብሮ በመስራት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸው ጥረቶች እንደሚጠናከሩም አረጋግጠዋል፡፡
በዞኑ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ የግብርና ስራውን ማዘመን ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ዋና አስተዳዳሪው አክለዋል፡፡
አካባቢው በስንዴ፣ በጤፍና በበቆሎ ምርት ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም በዘርፉ ከአካባቢው አልፎ ለሀገር የሚጠቅምና ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተው በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ገጠሩን ከከተማው ጋር በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ረገድ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ከህዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡