ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን በብልፅግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ነብዩ ስሑል ሚካኤል ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ነብዩ ስሑል ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (POA) ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በብሪክስ ባለብዙ ወገን ትብብር የአፍሪካን ድምጽ ከፍ ለማድረግ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ 30 በመቶ የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ የሚሳለጠው በዚሁ ቀጣና የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
ቀጣናው የበርካታ አካላት ፍላጎት ያለበት መሆኑንና ኢትዮጵያም ብሄራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቅ መልኩ ከሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደሆነ በመግለጽ።
የብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በመደመር እሳቤ እውን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነትና ተደማጭነት ከፍተኛ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
የልማት እቅዶችን ለማሳካት ከሀገራት ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ ከተናጠል ጥረት ይልቅ መደመር ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ማድረጓ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እውን እንዲሆን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ቀጣናዊ ድርጅቶች እንዲመሰረቱና የአፍሪካን አንድነት እንዲያጠናክር ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና መጫወቷን በመግለጽ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በታላቅ የዲፕሎማሲ ድል መጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ባለፈ የመላ አፍሪካ ኩራት መሆኑን ያነሱት አቶ ነብዩ፤ ግድቡ ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በብሪክስ ባለ ብዙ ወገን የትብብር መድረክ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ከራሷ አልፎ የአፍሪካን ድምጽ እያሰማች መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ በማጠናከር የልማት ዕቅዷንና ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ትሰራለች ብለዋል።