ቀጥታ፡

የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር በመሆን የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል-የቀድሞ ታጣቂዎች

ባሕርዳር፤ታሕሳስ 11/2018(ኢዜአ)፡-የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር በመሆን የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተን መጥተናል ሲሉ በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ ይዘው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ በመቀበል የተሀድሶ ስልጠና እየወሰዱ ወደ ማሕበረሰቡ መቀላቀላቸውን እንደቀጠሉ ነው።

በዚህም መሰረት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ላኮማ ወረዳ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በፈፀምነው ስሕተትና ባጠፋነው ጊዜ በመጸጸት ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰናል ብለዋል።

በሕዝብ ስም እየተማለ አምቡላንስን ማቃጠል፣ መሰረተ ልማቶችን ማውደም፣ ትምሕርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረግና ዘረፋ መፈፀም በቀጥታ ሕዝብን መጉዳት በመሆኑ ከጥፋታችን በመውጣት የሰላምን አማራጭ ተቀብለን መጥተናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል ዘመነ አዲስ እና ገደፋው ሞላ፤ በአብዛኛው በጫካ ሲንቀሳቀስ የነበረው ታጣቂ በተሳሳተ እሳቤ በጥፋት መንገድ ላይ መሆኑን በአግባቡ በመረዳት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በሕዝብ ስም እንታገላለን የሚል ማደናገሪያ ስለነበር ይህንኑ ሃሳብ በመቀበል ጫካ መግባታቸውን አንስተው በተግባር ሲታይ በሕዝብ ላይ ዘረፋ፣ እገታና ግዲያ መፈፀም በመሆኑ ይሕንን ተግባር በመቃወምና ሰላምን በመሻት መጥተናል ብለዋል።

በመሆኑም የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር በመሆን የበደልውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተን መጥተናል ሲሉ ተናግረዋል።

ሌሎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችም መንግስት ያቀረበውን የሰላም እድል በመጠቀም መጥተው ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲጀምሩ መክረዋል።


 

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ ጌታቸው ቢሻው፤ በዞኑ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማሕበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አሁንም ሙሉ ትጥቃቸውን ለመንግስት እያስረከቡ መግባታቸውን ቀጥለው እንዳሉ ጠቁመው፥ ይህም የሽፍታው ስብስብ እኩይ ተግባር በመገንዘቡ አብዛኛው የሰላም አማራጭን እየመረጠ ነው ብለዋል።

መንግስት በሆደ ሰፊነት አሁንም የሰላም በሩን ክፍት በማድረግ መቀበሉን እንደሚቀጥል አረጋግጠው፥በሰላም የሚገቡትን የተሀድሶ ስልጠና በመስጠት ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ የስራ እድል የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰላምን አማራጭ በማይቀበለው የሽፍታው ስብስብ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም