የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች በማልማት ጥቅም ላይ የማዋል ጥረት የተጨበጠ ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች በማልማት ጥቅም ላይ የማዋል ጥረት የተጨበጠ ውጤት እያመጣ ነው
ሀዋሳ፤ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች በማልማት ጥቅም ላይ የማዋል ጥረት የተጨበጠ ውጤት እያመጣ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ።
የትውልዱ የዘመናት ቁጭት የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን ከ14 ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ በስኬት ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ የተለያዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉባ ላይ ባደረጉት ንግግር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራት የሚጠግኑና ብልጽግናን የሚያፋጥኑ የተለያዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚከናወን ማብሰራቸው የሚታወስ ነው።
የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኒዩክሌር ኃይል ማብላያ፣ የግዙፍና ዘመናዊ ኤርፖርት ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ከተበሰሩት ውስጥ ዋናዎቹ ናቸው።
እነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ኢዜአ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁራንን አነጋግሯል።
በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ በዓሉ ጡቄላ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ወደ ስራ የገቡና እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የቀጣይ እጣ ፋንታዋን የሚወስኑ ናቸው ብለዋል።
ለአብነትም የማዳበሪያ ፋብርካ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን የመቻል ጥረትን ከማሳካት ባለፈ ለገበያ የሚሆን ትርፍ ምርት በማምረት ገቢ ለማግኘት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ጌታቸው አየለ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር እድገት ጽኑ መሰረት የሚያኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዘመናት ቁጭትን የመለሰው የህዳሴ ግድብና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ስራ መጀመራቸው የሀገር እድገትና ማንሰራራት ምልክቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች በማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት የሚታይ ብርሃንና ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል ብለዋል።