ቴክኖሎጂው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቴክኖሎጂው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ከህዋዌ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጠውን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግና ይበልጥ ለማዘመን የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከቻይናው ሁዋዌ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል፡፡
በዚህም፥ ስማርት ግሪድ ለማስፋፋት፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማዘመንና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ከህዋዌ ጋር በትብብር ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ኢንጅነር ጌቱ አክለውም፥ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ሁለቱም ተቋማት በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡
ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር ስርጭት መቆጣጠሪያ ለመገንባት፣ ለረጅም ጊዜ ኢነርጅ የሚያቆዩ ባትሪዎችን ለመትከልና የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን በኢትዮጵያ ለመተግበር ስምምነት ላይ መደረሱንም ጨመረው ጠቁመዋል፡፡
የሁዋዌ ኩባንያ ተወካዮች በበኩላቸው፥ በፈጠራ ላይ የተመሰረቱና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተላበሱ ዘላቂ የኢነርጂ መፍትሄ ቴክኖሎጂዎችን በኢትዮጵያ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ቴክኖሎጂን አውቆ የሚተገብር ሠራተኛን ለመፍጠር ክህሎት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችንም እንደሚያመቻቹም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም፥ አገልግሎቱ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመንና የደንበኞችን ቅሬታ ለመቅረፍ ጊዜውን የዋጀ ቴክኖሎጂ ለመተገበር የጀመረው ሪፎርም አካል መሆኑን ለኢዜአ ገልጿል፡፡