ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ የ10ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ከቀኑ 10 ሰዓት ፋሲል ከነማ ከነጌሌ አርሲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ፋሲል ከነማ በሊጉ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል አራቱን ሲያሸንፍ ድኑ በ17 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

አዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ እስከ አሁን በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ነጌሌ አርሲ በ13 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

በአዲስ አበባ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። 

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ባደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። በዘጠኙ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ግቦች ተቆጥረውበታል። 

ቡድኑ በሰባት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ በሶስቱ ሲያሽንፍ አራት ጊዜ ደግሞ ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ጎሎችን አስተናግዷል።

ቡናማዎቹ በ11 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። 

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ኢትዮጵያ ቡና ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታሉ።

በሌሎች መርሃ ግብሮች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከሸገር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ወላይታ ድቻ በሰባት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ሸገር ከተማ በ12 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ሃዋሳ ከተማ በ14 ነጥብ ሰባተኛ፣ የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ12 ነጥብ 16 ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም