በዞኑ የሕግ የበላይነትንና ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ሕብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሕግ የበላይነትንና ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ሕብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ቡሌ ሆራ፤ ታህሳስ 11/2018(ኢዜአ) ፡- በምዕራብ ጉጂ ዞን የህግ የበላይነትንና ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ሕብረተሰቡን ያሳተፉ የተቀናጁ ተግባራት ተጠናከረው መቀጠላቸውን የዞኑ አስተዳደርና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ አየለ ደንባ፣ የመንግስትን የሰላም አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች መመለሳቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።
ወደ ሰላም የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎችም የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ህይወት እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በቀጣይም በዞኑ የሕግ የበላይነትንና ሰላምን በዘላቂነት ለማስከበርና ለማፅናት ሕብረተሰቡን ያሳተፉ የተቀናጁ ተግባራት ተጠናከረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ክፍል ሀላፊ ምክትል ኢንፔክተር ፈዬራ ኬይረዲን፤ የቀድሞ ታጣቂዎች በየቀኑ ወደ ሰላም መንገድ እየመጡ መሆኑን አንስተዋል።
በተሳሳተ መንገድ ችግር ውስጥ ገብተው የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሕዝቡ ተከታታይ ጥረት ሲያደርጉ እንደቆዩ አውስተው ፤ ይህም ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን አስረድተዋል።
ከዞኑ ነዋሪዎች መካከል አባገዳ ጃርሶ ዱጎ፣ ከዞኑ ሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ከፍሎች ጋር በመሆን ለቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ባህልና እሴታቸውን እንዲሁም ቃላቸውን በማክበር እየተመለሱ በመሆኑ በዞኑ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል፡፡
ችግርን በውይይት ከመፍታት በስተቀር እርስ በእርስ በመጎዳዳት የሚገኝ ጥቅም፤ የሚመጣ ለውጥም የለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ወደ ሰላም ከተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል ሊበን ሸጋ በሰጠው አስተያየት፤ የሰላም አማራጭን ተቀብሎ በመመለስ የበደለውን ሕዝብ ለማካስ መዘጋጀቱን ገልጿል።
በጫካ የቀሩትም የሰላም መንገድ በመምረጥ ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱም መልዕክት አስተላልፏል።