ቀጥታ፡

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያላትን አጋርነት የማጠናከር ፍላጎት አላት -ተሰናባቹ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2018 (ኢዜአ)፦ ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ሽብርተኝነትን መዋጋትን ጨምሮ በቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላትን አጋርነት ለማጎልበት በጋራ መስራቷን እንደምትቀጥል ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና ገለጹ።

አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና የኢትዮጵያ እና ኬንያ የሁለትዮሽ ትብብር ጥልቅ የታሪክ ትስስር ያለው መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

ሀገራቱ የኬንያው የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት እና መስራች አባት ጆሞ ኬንያታ እና ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጊዜ አንስቶ ወዳጅነት እንደነበራቸው አውስተው ትብብሩ በከፍተኛ ደረጃ በሚደረጉ ጉብኝቶች እና ውይይቶች እየተጠናከረ መምጣቱን አመልክተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ጠንካራ አጋርነት ፈጥረው እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሶማሊያ በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ጨምሮ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ሰላም እና ደህንነት ለቀጣናው ዘላቂ ልማት ጠንካራ መሰረቶች ናቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እና የኬንያ የንግድ ትብብር እያደገ መምጣቱን የገለጹት ተሰናባቹ አምባሳደር የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የሀገራቱን የኢኮኖሚ ትብብሩን አድማስ የበለጠ እንደሚያሰፋው ነው የተናገሩት።

ቱሪዝም እና ንግድ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጎለብት ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የሁለቱ ሀገራት ቀጣናዊ ትስስር እንዲጎለብት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት የሚያስተሳስረው የ"ላፕሴት ፕሮጀክት" እና የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ጨምሮ በሌሎች መሰረት ልማት ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ትስስሩን የሚያሳልጡ ትልቅ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደር ጆርጅ ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማስመረቋ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉ ሲሆን ግድቡ በቀጣናው ሽግግርን የሚፈጥር ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1963 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቀጣናዊ መረጋጋት እና ደህንነት ፣ ንግድ እና የመሰረት ልማት ትስስር የሀገራቱ ዋንጫ የትብብር መስኮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም