ቀጥታ፡

ዘመን ገበያ የኢትዮጵያን ሰፊ የቆዳ ስፋትና ብዝሃ ምርት ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ ዘመን ገበያ የኢትዮጵያን ሰፊ የቆዳ ስፋትና ብዝሃ ምርት ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዘመን ገበያ በጋራ መስራት የሚችሉበትን አዲስ አሰራር ይፋ አድርገዋል።

ሁለቱ ተቋማት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ አምራቾችን ወደ ዘመን ገበያ በማስገባት ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገር ውስጥ ሸማቾች እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ፈርመውታል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ዘመን ገበያ የኢትዮጵያን ግብይት በዲጂታል ሥርዓት በማዘመን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሁሉን አቀፍና አካታች ማድረግ የሚያስችል ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለዲጅታል ኢትዮጵያ እውን መሆን ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ሰፊ የቆዳ ስፋትና ብዝሀ ምርት ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘመን ገበያ ምርትና አገልግሎቶችን በመላው ዓለም በማድረስ ተዓማኒነት ያለው የኤሌክትሮኒክ ግብይት ነው ብለዋል።

የዘመን ገበያ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ አስራ ሁለት ሺህ አይነት ምርቶች ገብተዋል፤ ደንበኞች ተመልክተውትም 70 ሺህ የሚሆኑት ግብይት ፈፅመዋል ብለዋል።

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በተደረገው ስምምነትም የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ውጤቶች፣ ኤሌክትሮኒክስና ቴክኖሎጂ፣ መድሀኒትና የህክምና ግብዓቶች፣ ኬሚካልና የግንባታ ግብዓቶች እና ሌሎችም የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች በዘመን ገበያ ለግብይት ይቀርባሉ ብለዋል።

ዘመን ገበያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት በአምራቾችና ሸማቾች መካከል መተማመንን በመፍጠር ቀልጣፋ ግብይት ማከናወን እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪዎች በመላ ሀገሪቱ ምርቶቻቸውን ለሸማቾች በቀጥታ የሚያቀርቡበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፤ ሸማቾች የሚፈልጉትን ምርት በአይነትና በጥራት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶች ዲጅታል ስርዓትን በመጠቀም ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡበትን ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

ዘመን ገበያ ከመነሻ ትዕዛዝ እስከ ግብይት ፍፃሜ ባለው የእሴት ሰንሰለት የሎጂስቲክስ፣ የትዕዛዝ አስተዳደር እና የዲጅታል ክፍያ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም