ዘመን ገበያ አምራችና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለመገበያየት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ዘመን ገበያ አምራችና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለመገበያየት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ ዘመን ገበያ አምራችና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ መገበያየት የሚያስችል መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዘመን ገበያ በጋራ መስራት የሚችሉበትን አዲስ አሰራር ይፋ አድርገዋል።
ሁለቱ ተቋማት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ አምራቾችን ወደ ዘመን ገበያ በማስገባት ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገር ውስጥ ሸማቾች እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ፈርመውታል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኤሌክትሮኒክ ግብይት በዓለም ዙሪያ ያሉ አምራቾችና ሸማቾችን በማገናኘት ቀልጣፋና ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እየፈጠረ ነው።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት በተደራጀ ሳይሆን በተበጣጠሰ መንገድ ሲከናወን እንደነበር አስታውሰው፤ ኢትዮ ቴሌኮም በዘመን ገበያ አማካኝነት ቀልጣፋ የግብይት ስርዓት እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት በማዘመን አምራቾችና ሸማቾች በቀጥታ በማገናኘት ለንግድ ስርዓቱ መሳለጥ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ዘመን ገበያ የንግድ ስርዓቱን በማዘመን በኢትዮጵያ መደበኛ የኤሌክትሮኒክ ግብይት መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተሟላ መሰረተ ልማት በማልማት በሚያስተዳድራቸው 14 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ200 በላይ ግዙፍ ኩባንያዎች እንዳሉ ገልጸዋል።
በዚህም ዘመን ገበያ አምራቾች ምርታቸውን በቀላሉ ለሸማቹ ማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸው፤ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች ማቅረብ ያስችላል ብለዋል።
ዘመን ገበያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ የጨርቃ ጨርቅ፣ ምግብ ነክ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ ግብዓትና ሌሎች ምርቶችን የገበያ ጉድለት መሙላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ከኢንዱስትሪዎች ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ ያስችላል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የአምራቾችና ሸማቾችን ተጠቃሚነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ቴክኖሎጂዎችን በማዳበር ለኢትዮጵያ ዲጂታል ሽግግር ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።