ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ዕድልን መግፋት በምንም መልኩ አዋጭ አይደለም

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተመቻቸውን የጠረጴዛ ዙሪያ ሀገራዊ ምክክር ዕድልን መግፋት በምንም መልኩ አዋጭ አይደለም ሲሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ(ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ግርማ ሰይፉ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ተግዳሮቶች ተቋቁማ ተዓምራዊ የዕድገት ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ(ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ግርማ ሰይፉ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አቶ ግርማ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ለዘመናት የቆየው የዜጎች የጭቆና ትግልና የህልውና ጥያቄ ነው።

በተለይም ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ የቀድሞው ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ የራሱንና የአባላቱን ጥቅም ለማስጠበቅ በዜጎች ላይ የፈጠረው ኢ-ፍትሐዊ አስተዳደር፣ ሕዝቡ በአደባባይ እንዲታገልና ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ግርማ፤ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የሀገራዊ ምክክር አውድ በመተው መሳሪያን በማንገብ የሚንቀሳቀሱ አካላት የዕውቀት አልባነት መገለጫ መሆኑን በጽኑ ተችተዋል።

ነፃነት ካመጣው የሰለጠነ የምክክር አውድ ባፈነገጠ መልኩ፣ በነፃነት ስም በመሳሪያና በጉልበት መጓዝን የመረጡ ኃይሎች መፈጠራቸው ለሀገር ልማት እንቅፋት መሆኑን ነው የገለጹት።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ የግጭት ሴራዎችን ተቋቁማ ያስመዘገበችው ውጤት አስደናቂ መሆኑንና ተዓምራዊ የዕድገት ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለች ሲሉ አብራርተዋል።

ኢዜማ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከር መፍትሔ ማምጣትን እንደ ቀዳሚ አማራጭ እንደሚቀበል ገልጸውም፤ የትጥቅ ትግልን በመተው በሐሳብ የበላይነት መወያየት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢዜማ ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የፖሊሲ አማራጭ ይዞ በመቅረብ፣ የአመራር አባላቱና ደጋፊዎቹ ለነቃ ፉክክር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑም አስታውቀዋል።

በምርጫ ቦርድ ዕውቅናው የተነሳው የቀድሞ ሕወሓት በክልሉ የሚያሳየው እብሪት መሠረተ ቢስና እውቀት አልባነትን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ የትግራይ ሕዝብ የፌዴራል መንግሥት ውክልናውን የሚያረጋግጥበትን አማራጭ እንዲፈጠርለት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራት ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአንድ አንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ኃይሎችን በተመለከተ ምርጫውን የማደናቀፍ አቅም እንደሌላቸው ነው የገለጹት።

የፓርቲያቸው የፖሊሲ አማራጮች ሌላውን የመጫን ፍላጎት እንደሌለው ጠቁመው፤ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሕዝብን በማስቀደም ለሀገር የሚጠቅም ውሳኔ ላይ መድረስ የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም