የሀገር ውስጥ የሴራሚክ ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ የሴራሚክ ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ የሀገር ውስጥ የሴራሚክ ምርት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚያስችሉ ፋብሪካዎች በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለፁ።
ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በቢሾፍቱ፣ በሞጆ እና በዱከም ከተሞች በሀገር ውስጥና በውጭ ባለሃብቶች በመገንባት ላይ ያሉና ስራ የጀመሩ የሴራሚክ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።
ፋብሪካዎቹ ለምርት አገልግሎት ከሚጠቀሙት ግብዓት 90 በመቶውን ከሀገር ውስጥ ማግኘታቸው በዘርፉ ውጤታማ ስራ ለማከናወን የላቀ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
ፋብሪካዎቹ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩ የግብዓት እጥረቶችን ለመፍታት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ካለው የሴራሚክ ፍላጎት 60 በመቶው በሀገር ውስጥ ምርት እንደሚሸፈን ጠቁመው፤ ቀሪው 40 በመቶ ከውጭ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ የፋብሪካዎቹ ስራ መጀመር በጉባ ብስራቶች ለመገንባት ለታቀዱት መኖሪያ ቤቶች የግብዓት አቅርቦት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የሀገር ውስጥ የሴራሚክ ምርት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚያስችሉ ፋብሪካዎች በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩም ተናግረዋል።
አንዱ ፋብሪካ በቀን እስከ ሃያ ሺህ ሜትር ካሬ ሴራሚክ የማምረት አቅም እንዳለው ጠቁመው ምርቶቹ ጥራታቸውን የጠበቁ በመሆናቸው ያላቸው ተፈላጊነት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ለመኖሪያና ለንግድ ቤቶች ግንባታ መሰረታዊ የሆኑት የሴራማክ ውጤቶች በተለይም ለግድግዳና ለወለል የሚውሉ ሲሆን፤ ፋብሪካዎቹ ለዚህ የሚያስፈልገውን ምርት ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም እንዳላቸው ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
የማዕድን ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸው፤ በተለይም ለግብርናው እድገት ወሳኝ የሆነውን ማዳበሪያ ለማቅረብ የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ምርት የሚገቡት ፋብሪካዎች የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ፋብሪካዎቹ ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ባሻገር ለውጭ ገበያ የሚውል በቂ ምርት የማምረት አቅም እንዳላቸውም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የግራንድየር ሴራሚክ ፋብሪካ ማርኬቲንግ ማኔጀር ኪሙንግ ፋንግ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በቻይና ባለሃብቶች መገንባቱንና ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም መሆኑ ለእውቀት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የካም ሴራሚክ ውጤቶች ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ተሻለ በልሁ ፋብሪካው በመንግስትና በግል ባለሃብት ትብብር መገንባቱን ጠቁመው የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን መጠቀሙ የውጭ ምንዛሪን ከማዳን ባሻገር ለኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።