በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል
አዲስ አበባ፤ ታሕሳስ 10/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ ማስቻሉ ተገለጸ።
የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል አባላት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የብረታ ብረት፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት፤ የክልሉ ኢንቨስትመንት ካውንስል ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ተዘዋውሮ በመመልከት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የዘርፍ አመራሮች ባለሙያዎችን ለረጅም ቀናት በኢንዱስትሪ አካባቢ በመንቀሳቀስ እንዲሚለከቱ መደረጉ ለኢንዱስትሪ እድገት አዋጭ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፤ በክልሉ አሻጋሪና ዘላቂ እቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪው ነው ብለዋል።
በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ያሳደገ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት 46 ነጥብ 4 በመቶ በ2017 ወደ 59 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም የበለጠ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅምና ወደ ምርት የሚገቡ ኢንዱስትሪዎችን ለማሳደግ የሚያስችል እድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚመቹ የፖሊሲ ማዕቀፎችና አሻጋሪና ዘላቂ የልማት እቅድ በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ተግባራት በቀጣይ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ለሚሰሩ ስራዎች አቅም ናቸውም ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል አባላት በክልሉ ባሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ምልከታ ማድረጋቸው የግሉ ዘርፍ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።