ሀዲያ ሆሳዕና ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ድል በመቀሌ 70 እንደርታ ላይ አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
ሀዲያ ሆሳዕና ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ድል በመቀሌ 70 እንደርታ ላይ አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሀዲያ ሆሳዕና መቀሌ 70 እንደርታን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጨዋታ ተመስገን ተስፋየ በ36ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ መቀሌ 70 እንደርታ መሪ ሆኗል።
ከእረፍት መልስ ተመስገን ብርሃኑ በ65ኛው እና በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ላይ ባሰረፋቸው ጎሎች ሀዲያ ሆሳዕናን አሸናፊ አድርጓል።
በ83ኛው ደቂቃ ላይ ለመቀሌ 70 እንደርታ ግቧን ያስቆጠረው ተመስገን ተስፋየ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው ሀዲያ ሆሳዕና በ10 ነጥብ ከ17ኛ ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቀሌ 70 እንደርታ በአምስት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ አላሸነፈም።
ዛሬ በተደረጉ የ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርባ ምንጭ ከተማን 3 ለ 1 ሲያሸንፍ ምድረገነት ሽሬ እና ባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።