በአባይ እና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ህጋዊና ተፈጥሯዊ የልማት ተጠቃሚነት መብቷ ሊከበርላት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአባይ እና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ህጋዊና ተፈጥሯዊ የልማት ተጠቃሚነት መብቷ ሊከበርላት ይገባል
ወልዲያ፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ በአባይ እና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ህጋዊና ተፈጥሯዊ የልማት ተጠቃሚነት መብት ማክበር እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።
በአንድ ወቅት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ለምንና በምን ምክንያት እንደሆነ በውል በማይታወቅ ሁኔታ ከባህር እንድትርቅ ሆናለች።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት በህልውናዋ ላይ አደጋ የደቀነ በመሆኑ የባለቤትነት መብቷ እውን እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የመሆን ህጋዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ መብት ያላት በመሆኑ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ባለቤትነቷን ለማሳካት እየተሰራ ነው።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን በአባይና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያ ህጋዊና ተፈጥሯዊ የልማት ተጠቃሚነት መብቷ ሊከበርላት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ማብሬ ታዴ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በቅርብ እርቀት እያለች የመግቢያ በር እንድታጣ መደረጉ ያስቆጫል።
በመሆኑም መልክዓ ምድራዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብቷን በመጠቀም የባህር በር ባለቤት መሆን አለባት በሚል የትውልድ ጥያቄ ሆኖ መምጣቱ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና እና የልማት ጥያቄ በመሆኑ ለስኬቱ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይገባናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት እና የዓሳ ሃብት እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ተፈጥሯዊ የመልማት መብቷን ተግባራዊ ማድረጓም ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን የመልማት መብት ለመጋፋትና የበይ ተመልካች እንድትሆን በግብጽ በኩል የሚደረገው ያልተገባ ጫና በየትኛውም የዓለም ህግ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ኑሩ አህመድ፤ ያለምክንያት የታጣው የኢትዮጵያ የባህር በር አሁን ላይ የሀገር ህልውና እና የትውልድ ጥያቄ ሆኖ መነሳቱ ተገቢ ነው ብለዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይ ከምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታው ባለፈ የቀጣናው የሰላምና ደህንነት ስትራቴጂክ ስፍራ በመሆኑ ኢትዮጵያ በባህሩ ላይ የጋራ ተሳትፎና የተጠቃሚነት ሚና ሊኖራት ግድ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ አባይን ለኤሌክትሪክ ሃይል ልማት በማዋል ዜጎቿን ከጨለማ ለማውጣት በምታደርገው ጥረት የግብጽ የማሰናከል ጥረት የራስን ሃብት የማልማት መብት የሚጋፋ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የመልማትና የመጠቀም መብት ማንም ሊነፍገው እንደማይችልና በሁሉቱ ውሃዎች ላይ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ እንደሚገባ ምሁራኑ ገልጸዋል።
በአባይ እና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያ ህጋዊና ተፈጥሯዊ የልማት ተጠቃሚነት መብቷን ማክበር የግድ መሆኑንም ነው የተናገሩት።