ወጣቱ የሀገር ሽማግሌዎችን ምክርና የሰላም ግንባታ እሴቶችን ተቀብሎ በመተግበር ለሀገር ልማት መትጋት አለበት--የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ የሀገር ሽማግሌዎችን ምክርና የሰላም ግንባታ እሴቶችን ተቀብሎ በመተግበር ለሀገር ልማት መትጋት አለበት--የሀገር ሽማግሌዎች
ባሕርዳር፤ታሕሳስ 10/2018(ኢዜአ)፡- ወጣቱ ትውልድ የሀገር ሽማግሌዎችን ምክረ ሀሳብና የሰላም ግንባታ እሴቶች ተቀብሎ በመተግበር ለሀገር ልማት ይበልጥ መትጋት እንዳለበት የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በዘላቂ ሰላም ግንባታ ዙሪያ በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ በጋራ ተወያይተዋል።
ከውይይቱ በኋላ ኢዜአ ካነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌዎች ከኦሮሚያ ክልል የመጡት አባ ገዳ ሀይሉ ለገሰ እንደገለጹት፤ የሽምግልና ስርዓትና የሰላም ግንባታ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሳሪያ ነው።
ወጣቱ ትውልድም ይህን የቆየ የኢትዮጵያዊያን የዳበረ ባሕላዊ እሴት በማክበርና በመቀበል ለሀገር አንድነት መፅናት ማዋል እንዳለበት መክረዋል።
የሀገር ሽማግሌዎችም የአባቶችን ታሪክና አደራ ተቀብሎ የሚሰራና ግብረገብ የሆነ ወጣት በማፍራት በኩል ሃላፊነታችን በአግባቡ መወጣት አለብን ብለዋል።
ከዘመናዊ ሕግ በፊት ጀምሮ ለዘመናት የዘለቀውን የሽምግልና ስርዓት በአግባቡ መጠቀም ላይ ክፍተት እየተስተዋለ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ ከጋሞ የመጡት አቶ ብርሃኑ ደባልቄ ናቸው።
ሽምግልና በሀገሪቱ የሕግ ጥላ ስር ሆኖ ችግሮች ሳይወሳሰቡ በአጭሩ መፍታት የሚያስችል የኢትዮጵያውያን እሴት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ወጣቱ በየአካባቢው ያሉ የቆዩ ችግር መፍቻ ባሕላዊ እሴቶችን እንደየ አካባቢው ሁኔታ የመረዳትና ለተግባራዊነቱ መትጋት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
የሀገር ሽማግሌ ለሰላም የሚተጋ፣ ለሀገር የሚቆረቆርና በዕድሜ ዘመኑ ያገኘውን ልምድ ተጠቅሞ ለእውነት የሚሰራ ነው ያሉት ደግሞ ከወላይታ የመጡት የሀገር ሽማግሌው አቶ ሰይፈ ለታ ናቸው።
ሽምግልና የሰላም መግቢያ በር ነው ያሉት አቶ ሰይፈ፤ ይህንን የተቀደሰ እሴት ወጣቱ ትውልድ ተቀብሎ በመንከባከብና በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት መክረዋል።
እርሳቸውም በአካባቢያቸው ለሚገኙ ወጣቶች በሃገር ሽማግሌዎች ሚና፣ በሽምግልና ስርዓት ምንነትና በሚያስገኘው ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ እየፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።