ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመለሰ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመለሰ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርባ ምንጭ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል።
አዲስ ግደይ በጨዋታ እና ፍጹም ቅጣት ምት ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዩጋንዳዊው ሳይመን ፒተር ቀሪዋን ጎል አስቆጥሯል።
ቡታቃ ሸመና ለአርባ ምንጭ ከተማ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ11 ነጥብ ከነበረበት 15ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ከፍ ብሏል።
በሊጉ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባ ምንጭ ከተማ በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ በሊጉ እስከ አሁን ምንም አላሸነፈም።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ምድረ ገነት ሽሬ እና ባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ባህር ዳር ከተማ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት መሳይ አገኘሁ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ምድረገነት ሽሬ በ14 ነጥብ ስምንተኛ፣ ባህር ዳር ከተማ በ13 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከሀድያ ሆሳዕና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።