በሰላም ዙሪያ እያከናወንን ያለውን ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን - የጎንደር ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በሰላም ዙሪያ እያከናወንን ያለውን ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን - የጎንደር ከተማ ወጣቶች
ጎንደር፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ የጎንደር ከተማ የሰላም ተምሳሌትነቷን ይዛ እንድትቀጥል የሰላም አምባሳደር በመሆን እያከናወኑት ያለውን ተግባር ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ የከተማው ወጣቶች ገለጹ።
በከተማው በሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ዮሐንስ ማሩ እንዳለው፤ በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የወጣቱን የወደፊት ተስፋ ለማሳካት መንገድ የከፈቱ ናቸው።
በተለይ በከተማው የተከናወኑ የኮሪደር እና የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራዎች የጎንደርን ታሪክና ውበት የገለጹና የባህል አውድ የፈጠሩ ዘመን ተሻጋሪ ተግባራት መሆናቸውን ተናግሯል።
በመሆኑም እነዚህ የልማት ሥራዎች የበለጠ ሰፍተውና አድገው እንዲቀጥሉ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
ወጣት መሃመድ አሊ በበኩሉ፤ በለውጡ መንግስት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የብልጽግና ጉዞ መገለጫና ማሳያ ናቸው ብሏል።
ጎንደር የሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት ተጠቃሚ ከሆኑ ከተሞች አንዷ በመሆኗ፤ ይህን ለማስቀጠል የሰላም አምባሳደር በመሆን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
በከተማዋ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በትኩረት እንደምትሰራ የገለፀችው ደግሞ ወጣት እመቤት ድረስ ነች፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የክልሉን ሰላም ለማጽናት በሚደረጉ ጥረቶች የወጣቱ ተሳትፎ የጎላ ነው።
ጎንደር ከተማ ታሪኳን በሚመጥን መንገድ በአመራሩ፣ በህዝቡና በወጣቱ የተቀናጀ ርብርብ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞች በምሳሌነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።
ወጣቱ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ በሪሁን መንግስቴ ናቸው፡፡
ታሪካዊ ጠላቶቻችን ዛሬም የውስጥ ጽንፈኛ ሃይሎችን መሳሪያ በማድረግ ኢትዮጵያን ለማዳከም ቢጥሩም አልተሳካላቸውም ሲሉ ተናግረዋል።
ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ መንግስት ህግ የማስከበር ተግባሩን ህብረተሰቡንና ወጣቱን በማስተባበር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር በለውጡ መንግስት ታሪኳ ታድሶ ዳግም ወደ ትንሳኤ ዘመን ተሸጋግራለች ሲሉ ተናግረዋል።
ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፣ መጪው የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር ወጣቶች በተደራጀ አግባብ ለሰላም መጽናት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።