ቀጥታ፡

የህፃናት መብትና ደህንነትን ለማስጠበቅ የተከናወኑ ቅንጅታዊ ስራዎች ውጤት አምጥተዋል

አዳማ፤ ታህሣሥ 10/2018(ኢዜአ)፦ የህፃናት መብትና ደህንነትን ለማስጠበቅ በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማምጣታቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኬይረዲን ገለፁ።

የህፃናትን  እንክብካቤና መብት ጥበቃን ለማረጋገጥ  ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ ተካሄዷል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኬይረዲን በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የህፃናት መብትና ደህንነት ለመጠበቅ የህፃናት ፓርላማ ከማቋቋም ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።

በቀዳማይ ልጅነት ዘመን ፕሮግራም በጤና፣ በስርዓተ ምግብ፣ በሁለንተናዊ እንክብካቤ፣ በትምህርትና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ በቅንጅት መሰራቱን አንስተዋል።

ህፃናት እንክብካቤ አግኝተው የትምህርት፣ የመዝናኛና የመጫወቻ ስፍራዎች እጥረትን ለመቅረፍም ከከተሞች ከፕላን ጋር እንዲካተት ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል። 

በሌላ በኩል በአቻና በሌሎች ገፊ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የሚወጡ ህፃናትን ከቤተሰብ ጋር የመቀላቀል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በአደራ ቤተሰብ እንዲያድጉ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሀምዲያ ሲራጅ በበኩላቸው በክልሉ የህፃናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ህፃናት ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ለአብነትም ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች በመጋለጥ ወደ ጎዳና የወጡ ህፃናት ወደ ቤተሰብ እንዲመለሱ  መደረጉን አንስተዋል።


 

በክልሉ ህገወጥ የህፃናት ዝውውርን ለመከላከል ከአደረጃጀቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ገነት በለጠ ናቸው።

በማህበራዊ ችግሮች ህፃናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ የቤተሰብን አቅም መገንባትና በኢኮኖሚ የማጠናከር ስራ መሰራቱንም  አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም