በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል
ነቀምቴ፤ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ) ፡- በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት የትምህርት ቤቶች ደረጃን ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የነቀምቴ ከተማ በኬ ጀማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ሁለተኛ ደረጃ የማሳደግ መርሀ ግብር የክልሉና የከተማዋ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በምክትል ሀላፊ ማዕረግ የቢሮው አማካሪ አቶ ኤፍሬም ተሰማ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት የትምህርት ቤቶች ደረጃን የማሻሻል ስራ ትኩረት ተሰጥቶት በተቀናጀ አግባብ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ወደ ሁለተኛ ደረጃ የሚያድገው የነቀምቴ ከተማ በኬ ጀማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚገኝበት ጠቁመው የትምህርት ቤቱን ደረጃ ለማሳደግ በ71 ሚሊየን ብር የማስፋፊያ ግንባታ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የትምህት ቤቱ ማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መቀበል አንደሚችልም አመላክተዋል።
የግንባታ ስራው በዘጠኝ ወር ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ጠቁመው የማስፋፊያ ግንባታው ኦቢኤም በተሰኘ የግንባታ ድርጅት የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል።
የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመገንባት የትምህርት ተቋማትን ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ማድረግ ይገባል ያሉት ደግሞ የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ መሰረት ሀይሉ ናቸው።
ትምህርት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እድገት መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
ተወዳዳሪ የተማረ የሰው ሀይል ለማፍራትም ከስር ኮትኩቶ ማሳደግ አስገዳጅ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት መሰጠቱን አስንተዋል።
ይህንን እውን ለማድረግም የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ከነቀምቴ ከተማ አስተዳደርና ትምህርት ቤቶች ፅህፈት ቤት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የበኬ ጀማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታም ለአመታት የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የነቀምቴ ከተማ ትምህርት ቤቶች ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጫላ ገመዳ የበኬ ጀማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መንግስት የህብረተሰቡን ጥያቄ የመለሰበት እንደሆነ ገልጸዋል።
የነቀምቴ ከተማ የበኬ ጀማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታም የተማሪ ክፍል ጥመርታን የሚያሻሽለው መሆኑን አመላክተዋል።
የትምህርት ቤቱ ደረጃ ማደግ አስመልክቶ አስተያየታቸውን ከሰጡ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የቀበሌ 06 ነዋሪ አቶ ፍቃዱ ደበሌ በከተማዋ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ በሚከናወነው የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻሉ ተግባር ህብረተሰቡ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወይዘሮ ኢትዬ በሻ በበኩላቸው የማስፋፊያ ግንባታው ልጆቻችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቅርበት እንዲያገኙና ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር እድል ይከፍታል ብለዋል።