ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ቢላሉል ሐበሺን ጎበኙ 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መካኒሳ አካባቢ የሚገኘውን ቢላሉል ሐበሺን ዛሬ ጎብኝተዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ቢላሉል ሐበሺ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል የሆነውን የኢትዮጵያን የእስልምና ጉዞ ከመነሻ እስከ አሁን የሚያሳይ ሙዝየም ማደራጀቱን ገልጸዋል። 


 

በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክን የሚዘክሩ ሙዝየሞች በጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸው፣ ይህ ሙዝየም ታላቅ ዋጋ ያለው ነው ብለዋል። 

በዚህ ሙዝየም ውስጥ ከመጀመሪያው ሂጅራ አንሥቶ ያለው ታሪክ እንደሚታይ ገልጸው ይህም ኢትዮጵያ የብዙ ሶሐባዎች ማረፊያ፣ የታላላቅ ዓሊሞች መገኛ እና የአስደናቂ እስላማዊ ቅርሶች መናኸሪያ እንደሆነች የሚያመላክት እንደሆነ ተናግረዋል። 


 

ተቋሙ ወጣቶችን በሙያ አሠልጥኖ ለሥራ በማብቃት፣ ችግረኞችን በመርዳት፣ ጥናትና ምርምርን በመደገፍ፣ ለወጣቶች ተስማሚ መዋያ በማዘጋጀት እና የሚያደርገው አስተዋጽዖ እጅግ ታላቅ ነው ሲሉም አድንቀዋል። 

ቢላሉ ሐበሺ ዕድሮች አሁን ከያዙት ዓላማ በላይ በማከናወን የማኅበረሰብን ሕይወት ሊቀይሩ እንደሚችሉ አርአያ የሚሆን ተቋም መሆኑን አመልክተዋል። 


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋሙን በማገዝ ታሪካችንን እንድንጠብቅና ወጣቶቻችንን እንድናበቃ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም