ቀጥታ፡

ለህዝብ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ይሰራል- የካፋ ዞን አስተዳደር

ቦንጋ ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ ከህብረተሰቡ ለተነሱ መሰረታዊ የልማት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት በተቀናጀ  አግባብ  እንደሚሰራ የካፋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ከሰሞኑ "የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በቦንጋ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ህዝባዊ የውይይት መድረክ መካሄዱ የሚታወስ ነው። 

መድረኩን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ እንደገለጹት፤ ውይይቱ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን መተማመን ከፍ ያደረገና በርካታ ጠቃሚ ሀሳቦች የተገኙበት ነው፡፡

መንግስት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው የህዝብን ሀሳብና ፍላጎት ማዳመጥና ተናቦና ተቀራርቦ መስራት መሆኑን ገልጸዋል።

ውይይቱ ከወትሮ በተለየ መልኩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ሀሳቦች የተንሸራሸሩበት እንደነበር አስታውሰው፤ በሀገር፣ በክልል፣ በዞንና በከተማ ደረጃ ለተመዘገቡ የልማት ውጤቶች ህዝቡ እውቅና የሰጠበት መሆኑን አንስተዋል።

በተለይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እንዲሁም በገበታ ለሀገርና ለትውልድ መርሀ ግብር የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ የመደመር መንግስት ውጤቶች መሆናቸውን አንስቷል ብለዋል።

የጉባ ብስራቶች የሆኑት የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የኒውክሌር ሀይል እና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ለስኬታቸው ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንደሚቆም አጋርነቱን ያሳየበት መድረክ እንደነበርም አቶ እንዳሻው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የባህር በር ባለቤት ለመሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት ህዝቡ እንደሚደግፍም በሰፊው በመድረኩ መነሳቱን አቶ እንዳሻው አንስተዋል። 

በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችና በቦንጋ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የህዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለገጽታ ግንባታ እያገዘ መሆኑንም በመድረኩ መነሳቱን አቶ እንዳሻው ተናግረዋል።

በአንጻሩ የቦንጋ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር፣ ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈው ዋና የአስፋልት መንገድ በደረሰበት ጉዳት ከአገልግሎት ውጪ መሆንና የቦንጋ አየር ማረፊያ ግንባታ መዘግየት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ህዝቡ ማንሳቱን ነው የገለጹት።

በተጨማሪም በዞኑ አንድም የኢንዱስትሪ ፓርክ አለመኖር እንዲሁም የዲሪ ማሻ፣ የሺሺንዳ ቴፒ አስፋልት መንገድ ግንባታ ጉዳይ  በመድረኩ ከተነሱ የልማት ጥያቄዎች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።

ለእነዚህ መሰረታዊ የልማት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፣ በቀጣይም እነዚህ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል'

በተለይ በዞኑ አቅም የተጀመሩ የመንገድ፣ የድልድይና የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም