በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ወልቂጤ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ):- በጉራጌ ዞን የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት በተቀናጀ መንገድ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ ።
በዞኑ በወልቂጤ ከተማ ''የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች'' በሚል መሪ ሃሳብ በተደረገው የህዝብ ውይይት የተነሱ የልማት ጥያቄዎችን በተቀናጀ መንገድ በመመለስ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በጉዳዩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት፤ በዞኑ የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረትና በተቀናጀ አግባብ እየተከናወኑ ነው፡፡
እነዚህ በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት በተቀናጀና አሳታፊ በሆነ መንገድ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
ውይይቱም ህብረተሰቡና አስተዳደሩ የልማት ጸጋዎችን በተቀናጀ መንገድ ወደ ውጤት ለመቀየር የጋራ መግባባት የተደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የገጠርና ከተማ ኮሪደር ልማት፣ የመስኖ፣ የእንስሳት ሀብትን ጨምሮ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ አዳዲስ የልማት ኢኒሺዬቲቮች የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በተለይም በዞኑ በከተሞች እና በገጠር በተቀናጀ መንገድ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች የአካባቢን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ የህብረተሰቡ የኑሮና የሥራ ባህል እንዲሻሻል ማስቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ሀገራዊ የልማትና ብልጽግና ግቦችን ለማሳካት የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች እንዲሳኩ የሚደረገው ተሳትፎም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ላይ መደረሱንም አንስተዋል።
የትውልዱ ቁጭት የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ያለምንም ልዩነት የተደረገው ርብርብ፣ ትብብርና መደጋገፍ ያስገኘውን ድል በሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚጠናከር በመድረኩ መገለጹን ተናግረዋል።
መድረኩ ህዝቡ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንዲሁም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ያጣነውን የባህር በር ለማስመለስ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ ስለመሆኑ የገለፀበት ነው ብለዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር የግብርናውን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ህብረተሰቡ በንቃት እንደሚሳተፍ ቃል የገባበት እንደሆነም አክለዋል።
የከሬብ መስኖ ፕሮጀክት፣ የወልቂጤ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ የተነሳውን ጥያቄም በረጅምና በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በመንግሥት እና ሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር የሚፈታተኑ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረትም ከህዝብ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡