የዓባይ ተፋሰስ አገራትን በማግለል እኔ ብቻ ልወስንና ልጠቀም የሚለው የግብፅ የቅኝ ግዛት እሳቤ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓባይ ተፋሰስ አገራትን በማግለል እኔ ብቻ ልወስንና ልጠቀም የሚለው የግብፅ የቅኝ ግዛት እሳቤ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ የዓባይ ተፋሰስ አገራትን በማግለል እኔ ብቻ ልወስንና ልጠቀም የሚለው የግብፅ የቅኝ ግዛት እሳቤ በዚህ ዘመን የማይሰራና በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የውሃ ተመራማሪ ምሁራን ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በበርካታ ጫናዎች ውስጥ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ቁርጠኝነት ከ14 ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ መመረቁ ይታወቃል።
ከጅምሩ አንስቶ የግድቡን የግንባታ ሂደት ለማስተጓጎል ጫና ስታደርግ የቆየችው ግብጽ ዛሬም በሀሰተኛ መረጃና አሉባልታ በማሰራጨት ዓለም አቀፉን ማህበረሰቡን የማደናገር ጥረቷን ቀጥላበታለች።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ቢበቃም የግብጽ ፕሮፓጋንዳ እና የማደናገሪያ ሃሳብ መቀጠሉ ለምን ስንል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ዘርፍ ተመራማሪዎችን ጠይቀናል።
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር እና የስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል የውሃ ገብ አካላት ተመራማሪ ምህረት ደናንቶ (ዶ/ር)፤ የዓባይ ተፋሰስ አገራት ውሃውን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት ቢኖራቸውም በግብጽ በኩል ግን ዓባይን ከእኔ በላይ የሚጠቀምና በውሃው ላይ የሚወስን ሀገር ሊኖር አይገባም የሚለው የቅኝ ግዛት እሳቤዋን ዛሬም ድረስ ቀጥላበታለች ብለዋል።
ከ86 በመቶ በላይ የዓባይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ሃብቷን አልምታ የመጠቀም መብት እንዳላት እየታወቀ በግብጽ በኩል ግን የኢትዮጵያ መልማትና ተጠቃሚነት መኖር የለበትም የሚለው አቋሟ እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓባይና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የመልማትና የመጠቀም መብት ሊከለክል የሚችል ዓለም አቀፍ ህግ ባለመኖሩ በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ የልማትና ተጠቃሚነት መብቷን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የግብጽ የእኔ ብቻ ልጠቀም የሚለውና ሌሎችን የማግለል የቅኝ ግዛት እሳቤ በዚህ ዘመን የማይሰራና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።
በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የግብጽ የማደናቀፍ ጥረትና ጫና ሳይሳካ ቀርቶ የግድቡ ግንባታ በስኬት በመጠናቀቁና የዲፕሎማሲ ኪሳራም ጭምር ስለገጠማት አሁንም የተለያዩ ማደናገሪያዎችን ይዛ ቀጥላለች ብለዋል።
የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት አልምቶ የመጠቀም እድል ለማሰናከል ግብጽ በተሳሳተ ስሌት የምታደርገው እንቅስቃሴ በዚህ ዘመን በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ምሁሩ ተናግረዋል።
በመሆኑም የግብጽ ፖለቲከኞች ከማደናገሪያ ሃሳብ በመውጣት በቀናነት ለፍትሃዊ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የውሃ ሀብትና ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ቴዎድሮስ አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የግብጽ የማደናቀፍ ጥረት በኢትዮጵያዊያን ብርታት ቢከሽፍም አሁንም በሌሎች የማደናገሪያ ሃሳቦች መቀጠሏን ገልጸዋል።
የግብጽ አሁናዊ የፖለቲካ አካሄድ ከሳይንስና እውነታ የራቀና በዚህ ዘመንም ከቅኝ ግዛት እሳቤ ያልተላቀቀ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ለአፍሪካውያን ውስብስብ ችግሮች አንዱ ምክንያት በቅኝ ገዢዎች የተሰጠ ትርክት መሆኑን አስታውሰው በዚህ ረገድ የግብጾች የተሳሳተ ትርክትና ስሌት አሁንም የቀጠለ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ከግለኝነትና የማደናገሪያ እሳቤ በመውጣት ትብብርንና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋገጥ መልኩ ተቀራርቦ መስራት ይገባል ብለዋል።
በሕዳሴው ግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮችን በመግፋት የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብን ለማራመድ በግብጽ መንግስት ባለስልጣናት የሚደረገው ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታ ጋር የማይሄድ መሆኑን የኢፌደሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው።