የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል- ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል- ተገልጋዮች
ወላይታ ሶዶ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ በወላይታ ዞን የአረካ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
መንግስት በሁሉም የህዝብ አገልግሎት ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ የመሶብ አንድ ማዕከልን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን ዘመናዊና ዲጂታል እያደረገ ይገኛል።
በተለይም የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሠጣጥን ለማዘመን የኦን ላይን አገልግሎት ተግባራዊ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት በወላይታ ዞን የአረካ ከተማ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ በመመልከት ተገልጋዮችን አነጋግሯል።
በአገልግሎቱ ዙሪያ አስተያየት የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎችም የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ መደረጉ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።
ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ ማቴዎስ ማሞ እና አቶ ሚልዮን አዲሱ፤ ከዚህ ቀደም እንግልትና ምልልስ የነበረባቸው ዘርፎች በመዘመናቸው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የዲጂታል አገልግሎት ጊዜን ገንዘብንና ውጣ ውረድን የሚያስቀር በመሆኑ በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።
የአረካ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ካሳ፤ የማዘጋጃ ቤትን አገልግሎት በማዘመን ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የተገልጋዮችን እንግልት ለማስቀረትና ብልሹ አሰራርን ለመግታት ጭምር የዲጂታል አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን አንስተው ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።