ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ የኃይልና የብርሃን በረከት ሆኗል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ የኃይልና የብርሃን በረከት ሆኗል ሲሉ የግድቡ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የሀገራት መሪዎች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መመረቁ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤቶቿና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የመላው ጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ የሚቀይር መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግድቡ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በከፍተኛ መጠን በማሳደግ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በዚህም ለሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ኃይል እንዲያገኝ በማድረግ ለአገር ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን የይቻላል ህያው ምልክት መሆኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ክፍሌ፥ በረከቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለቀጣናውና ለአፍሪካ መድረስ ጀምሯል ብለዋል።

ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ትስስርን ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ የብርሃን ምንጫቸው እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁመው ያሳኩት የጽናትና የአሸናፊነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይ ለሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መሰረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል።

ከገንዘብ ባለፈ የህይወት ዋጋ ተከፍሎ የተገነባና በጋራ ደማቅ አሻራ የተጻፈበት ግድብ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም