የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን እናጠናክራለን- አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን እናጠናክራለን- አመራሮች
ወልዲያ ፤ታሕሳስ 10/2018(ኢዜአ)፡- የመደመር መንግስት እሳቤዎችን በመተግበር የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ገለጹ።
የመደመር መንግስት እሳቤ ላይ የወሰዱት ስልጠና ክፍተቶቻቸውን በማስተካከል ሀገር አሻጋሪ የልማት ስራዎችን በመተግበር የሕዝቡን ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አቅም እንደፈጠረላቸው አመራሮቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ አመራሮች መካከል የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ንጉስ ዝናቡ እንዳመለከቱት፤ስልጠናው አመራሩ የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎትን ለማሟላት በቁጭት እንዲነሳሳ አስችሎታል።
አመራሩ ጊዜውንና ዕውቀቱን በማቀናጀት ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መነቃቃት የፈጠረ ነውም ብለዋል።
ለአብነትም የሰላም ግንባታ ፣ ትውልድን በትምህርት የመቅረጽ፣ በጤና ፣ በከተማ ግብርናና በስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በመደመር መንግስት እሳቤዎች እንደሚቃኙ ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማትን ይበልጥ ከፍ አድርጎ በመስራት የከተማዋን ገጽታ በመለወጥ ውብና ጽዱ እንድትሆን እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል።
ሕብረተሰቡ በተለያዩ መድረኮች ያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት ከስልጠናው ትልቅ አቅም የፈጠረ ግንዛቤ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጌታቸው ናቸው።
በተለይም በጤና መድህንና በመደበኛ ህክምና አገልግሎት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ይበልጥ ቁርጠኛ እንድንሆን አስችሎናል ብለዋል።
በዘርፈ ብዙ የጤና ስራዎች ሕብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል በየደረጃው ከሚገኙ ሰራተኞች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ በመደመር መንግስት እሳቤ ወደ ስራ መገባቱን ነው ያብራሩት።
የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወንድሙ በበኩላቸው፤ ገበያን በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን ማርገብ የሚያስችል ጠንካራ የድጋፍና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የገበያ ማዕከልን ማስፋፋትን ጨምሮ ሌሎችም ሕብረተሰቡና አምራቹ በቀጥታ የሚገናኙበት አሰራሮች መዘርጋታቸውን ጠቅሰዋል።
የመደመር መንግስት እሳቤዎች ሰው ተኮር በመሆናቸው የከተማዋ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎቶች ለማሟላት ስልጠናው ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸውም አውስተዋል።
በመደመር መንግስት እይታና እሳቤዎች መሰረት ሰላምን ጠብቆ በማፅናት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ለማሟላት ተግተው እንደሚሰሩ አመራሮቹ ገልጸዋል።