በሐረር የተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ለልማትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ የጋራ አቋም የተወሰደበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር የተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ለልማትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ የጋራ አቋም የተወሰደበት ነው
ሐረር፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ በሐረር የተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ለልማትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ የጋራ አቋም የተወሰደበት መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌቱ ወየሳ ገለጹ።
የሀረሪ ክልልን ጨምሮ በአዲስ አበባና የተለያዩ የክልል ከተሞች "የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው ይታወቃል።
በመድረኮቹ በመንግስት የተጀመሩ ተስፋ የተጣለባቸው የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉ፣ ለሰላምና መረጋጋት በትኩረት መስራት፣ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትን መግታት ላይ ከተሳታፊዎች በብዛት ተነስተዋል።
በመሆኑም በሀረር ከተማ ከተካሄደው መድረክ ምን ምን መሰረታዊ ነጥቦች ተነሱ? በሚለው ላይ ኢዜአ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌቱ ወየሳን አነጋግሯል።
በተካሄደው ውይይት ህዝቡ የልማቱና የሰላም ግንባታ ባለቤት መሆኑን በተግባር ያሳየበት እንዲሁም ለመንግስት ጥሩ ጅምሮች እውቅና የሰጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ከመልካም አስተዳደር፣ ከመሰረተ ልማት፣ ሰላምን ከማጽናት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና ከሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ህዝቡ ተሳትፎውን ያሳየበትና ለተከናወኑ ስራዎችም እውቅና የሰጠበት ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር የማድረስ፣ በጎዶሎነት የተነሱትን የማረምና ለህዝብ የላቀ ተጠቃሚነት ለመትጋት አመራሩ ቃል የገባንበት መሆኑን ገልጸዋል።.
መንግስት ለጋራ ልማትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት በመትጋት ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ መሆኑን አንስተውም ከህዝብ የተገኙ ግብአቶችን በመሰነቅ በየደረጃው ያለው አመራር ለላቀ ስኬት ለመስራት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ህዝቡ እያደረገ ላለው የላቀ አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይ ለሚከናወኑ ስራዎችም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።