ቀጥታ፡

በጊምቢ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ንጹህ አካባቢን ፈጥሯል

ጊምቢ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በጊምቢ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የቆሻሻ አወጋገድ ክፍተቶች በማረም ንጹህ አካባቢ እንዲኖረን አድርጓል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ውብ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ የነዋሪዎችን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ ስለመምጣቱም አክለዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኢዶሳ ገቢሳ፤ የኮሪደር ልማቱ በአካባቢያቸው ያለውን ሀብት እንዲገነዘቡ ከማድረግ ባለፈ ንጹህና ለኑሮ ምቹ አካባቢ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ 


 

በኮሪደር ልማት ስራው ልዩ የእግረኛ መንገድ፣ ንጹህ አረንጓዴ ስፍራና ውበትን የሚጨምሩ የመንገድ መብራቶች ዝርጋታ በመከናወኑ ለነዋሪዎች በእግር ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡  

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ ውበትን እንድትጎናጸፍ እና በአኗኗር ዘይቤያችን ላይ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ያሉት ደግሞ  የከተማዋ ነዋሪ ላሊሳ ቡልቲ ናቸው።  


 

በተጨማሪም የልማት ስራው ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የቆሻሻ አወጋገድ ክፍተቶችን በመቅረፍ ንጽህናው የተጠበቀ፣ ተስማሚና ውብ አካባቢ እንዲኖረን አስቸሏል ብለዋል፡፡

ሸህ ሁሴን ጌታሁን የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፤የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቀየር ውበትን እንድትጎናጸፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡


 

የጊምቢ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አቶ ፈዬራ አቦማ፤በከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ቀሪ ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶች እንዲሁም አረንጓዴ ስፍራዎችን አካቶ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን ወደ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።


 

በተለይም የኮሪደር ልማት ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በላይ ከዩኒቨርሲቲዎች ለተመረቁ ወጣቶች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን  በተገቢው በመተገበር ገቢ እንዲያገኙ እያስቻለ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የጊምቢ ከተማን ለኑሮ፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ከንቲባው አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም