የሸማች ማህበራት ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሸማች ማህበራት ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሸማች የህብረት ስራ ማህበራት በተመጣጣኝ ዋጋ በሚያቀርቡት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ሸማቾች ገለጹ፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አቶ አበራ ተሰማ እና ወይዘሮ በላይነሽ ሸንቁጥ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን ለመሸመት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ በአቅራቢያቸው የሸማች ማህበራት እንዲስፋፉ መደረጉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
የማህበራቱ መበራከት ለሸማቹ ትልቅ እፎይታ ከመፍጠሩም በላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከሚያደርጉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በመጠበቅ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል ።
አቶ ጥላሁን ኃይሌ የተባሉ ሸማች በበኩላቸው፤ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የማህበራቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ፤ በስኳርና በዘይት አቅርቦት ላይ የሚታዩ ውስንነቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የደራሽ ለመርካቶ ሸማች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ገብሬ እና ብርሃን ለህዝብ ሸማች ማህበር የሰው ኃይል አስተዳደር መቶ አለቃ ባዬ ዳምጠው፤ በአንዳንድ ምርቶች አቅርቦት ላይ የሚታዩ እጥረቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በመዲናዋ የሚገኙ የሸማች ማህበራት መበራከት ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሸታዬ መሐመድ፤ በአሁኑ ወቅት በመጋዘኖች ውስጥ በቂ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ክምችት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
በአንዳንድ ምርቶች ላይ የሚታየውን እጥረት ለመፍታትና አቅርቦቱን ለማሳደግ ከአምራቾችና ከአከፋፋዮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
መንግስት የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል የምርት አቅርቦትን በመጨመር በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ከሸማች ማህበራት በተጨማሪ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መደረጉንም ገልጸዋል።