የትግራይ ክልል ህዝብን የምክክር እድል በመግፋት የሰላም እንቅፋት መሆን ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል ህዝብን የምክክር እድል በመግፋት የሰላም እንቅፋት መሆን ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው
ሽሬ፤ ታህሳስ 10/2018(ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል ህዝብን የምክክር እድል በመግፋት የሰላም እንቅፋት መሆን ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን በክልሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች እና የአጀንዳ ልየታ በማከናወን የምክክር ምእራፉን እያካሄደ ይገኛል።
በዚህ የምክክር ሂደት በዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮች ላይ በመምከር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የመፍጠር አላማ በመሰነቅ ዜጎች በንቃት እየተሳተፉበትም ነው።
በዚህም መሰረት የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን በ11 ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊዎችን ለይቶ አጀንዳቸውን ተቀብሎ ቀሪዎችንም በተመሳሳይ ለማሳተፍ በመስራት ላይ ይገኛል።
በትግራይ ክልልም የምክክር ሂደቱን ለመጀመር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየሰራ በመሆኑ ከዚህ አንፃር የህዝቡን የምክክር መሻት በተመለከተ ኢዜአ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።
በአስተያየታቸውም የትግራይ ክልል ህዝብ ፍላጎት ከምንም በላይ ዘላቂ ሰላምና ልማት በመሆኑ በሀገራዊ ምክክሩ የመሳተፍ ፍላጎትና ዝግጁነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ህዝብ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ እንዳይሳተፍ እድሉን በመግፋት የሰላም እንቅፋት መሆን በፍፁም ተገቢነትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አስተያየታቸውን ከሰጡ መካከል ኢንጂነር አብርሃ እምባፍራሽ፤ የትግራይ ክልል ህዝብ እንደሌሎቹ የሀገሪቱ ክልሎች ህዝቦች ሁሉ አጀንዳውን አቅርቦ በሀገሩ ጉዳይ መምከርን ይሻል ብለዋል።
በምክክር የሀገርን ችግሮች መፍታት መልካም ስለመሆኑ አንስተው ይህንን መልካም አጋጣሚ በመግፋት ህዝብ የእድሉ ተጠቃሚ እንዳይሆን መስራት ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር እድልን በማሰናከል የራስን የፖለቲካ ፍላጎት የማራመድና የሰላም እንቅፋት መሆንም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ መምህርት አስቴር ካሳሁን፤ የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እድል በመሆኑ በንቃት መሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ስለሆነም የትግራይ ክልል ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እድሉን በመጠቀም አጀንዳውን ሊያቀርብና ሊመክር ይገባል ብለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑን ጥረት በማገዝ በመመካከር ለሀገራዊ ችግሮች የመፍትሄው አካል በመሆን ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር መምህር ፀጋዛአብ ካሕሱ፤ በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ሰላምን ለማጽናትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ከምክክር በላይ መፍትሄ ሊኖር አይችልም ብለዋል።
የትግራይ ክልል ህዝብ ፍላጎትም ከምንም በላይ ዘላቂ ሰላምና ልማት በመሆኑ በሀገራዊ ምክክሩ በመሳተፍ አጀንዳውን አቅርቦ በሀገር ጉዳይ መክሮ የመፍትሄው አካል ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለህዝብ የመጣን እድልና የምክክር አጀንዳ በመግፋት “እኔ አውቅልሃለሁ በሚል የግል ፍላጎትን በሃይልና በጦርነት ለማሳካት መሞከር ጊዜውን የማይመጥን ያረጃ አስተሳሰብ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አብርሀ አከሎም፤ በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በምክክር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
የትግራይ ክልል ህዝብ እንደ ሌሎች ክልሎች ህዝቦች በተሟላ መንገድ በምክክሩ አጀንዳውን ማቅረብና መሳተፍ አለበት ብለዋል።
ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ መሳካት ኢትዮጵያውያን በያለንበት የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በይፋ ከተቋቋመ ጀምሮ ከዝግጅት ምእራፍ ተነስቶ በምክክር ምእራፍ እስካሁን በርካታ ተግባራትን ማከናወኑ ይታወቃል።