በዞኑ ከ251 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ251 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል
ጊምቢ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ከ251 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን ተገለጸ፡፡
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ከ33 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ዘንድሮም ይኸው ተግባር በተለያዩ ክልሎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ሲሆን በኦሮሚያ ክልልም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው አርሶ አደሮችን ባሳተፈ መልኩ እየተካሄደ ነው።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆን መሬትን ወደ ልማት እንዲገባ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማጎልበት ስራ ተሰርቷል።
አሁን ላይም በክልሉ በሚገኙ ዞኖች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ሲሆን ከነዚሁ ዞኖች አንዱ በሆነው በምዕራብ ወለጋ ዞን በተያዘው የበጋ ወራት ከ251 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር መሽርሸርን በማስቀረት፣ የከርስ ምድርና ገጸ ምድር ውሀ ሀብት በመጨምርና የግብርና ምርታማነት በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል፡፡
በዘንድሮ በጋ ወራትም በ251 ሺህ 471 ሄክታር መሬት በላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው በስራውም ከ400 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ አክለዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ የእርከን ስራዎች፣ የውሃ መቀልበሻ ቦዮችና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡
ስራውን ለማሳካትም ካለፉት ዓመታት የተገኙ ልምዶችን በመቀመር የህብረተሰብ ንቅናቄ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
ባለፉት ጊዜያት በተከናወኑት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ከልማት ወጪ የነበሩ አካባቢዎች ዳግም ወደ ልማት መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአካባቢዎቹ መልማትም ህብረተሰቡ አካባቢውን እየጠበቀ ከልማቱ ጋር የተሳሰሩ እንደ የንብ ማነብ፣ የከብቶች መኖ ልማት እና ሌሎች የልማት ተግባራትን እንዲያከናውን ዕድል እንደተፈጠረለት ገልጸዋል።