ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአዳማ ከተማ ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።

ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 

በጨዋታዎቹ ላይ 11 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 21 ጎሎችን አስተናግዷል። አዳማ ከተማ በ15 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ 11 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። 30 ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሊጉን በ33 ነጥብ እየመራ ነው።  በ12ኛ ሳምንት የወቅቱን የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ለ 0 መርታቱ የሚታወስ ነው። 

ቡድኑ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። አዳማ ከተማ በሊጉ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሃዋሳ ከተማ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 22 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በ26 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባካሄዳቸው 10 ጨዋታዎች ስምንቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። 27 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ25 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። 

ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው ላይ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም