የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ10ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ይመለሳል።
ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎችን አስተናግዷል።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ያሸነፈው ጨዋታ የለም። አራት ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። አራት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል።
አርባምንጭ ከተማ በአምስት ነጥብ 19ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ አሸናነፊነት መንገድ ለመመለስ፣ አርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይጫወታሉ።
በሌላኛው መርሃ ግብር ምድረገነት ሽሬ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምድረገነት ሽሬ በሊጉ ባከናወናቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች በሶስቱ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በዘጠኙ ጨዋታዎች ላይ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ13 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሊጉ ካካሄዳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ያሸነፈው ባህር ዳር ከተማ በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረውበታል። ባህር ዳር ከተማ በ12 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከሀዲያ ሆሳዕና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በአምስት ነጥብ 19ኛ እና ሀዲያ ሆሳዕና በሰባት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
ጨዋታው መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት፣ ሀዲያ ሆሳዕና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና በ20 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ሀዲያ ሆሳዕና፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ መቀሌ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ ከ17ኛ እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።