ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በክብር ተቀብላ በማስተናገድ በአርዓያነት የሚወሰድ ሚና እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በክብር ተቀብላ በማስተናገድ በአርዓያነት የሚወሰድ ሚና እየተወጣች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን "ፍልሰተኞችን እናክብር፣ የወደፊት ህይወታቸውን በጋራ እንቅረፅ" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሳይንስ ሙዚየም ተከብሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ስደተኞች በሄዱባቸው ሀገራት ለብዝበዛ እና ለአስከፊ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ስደተኞች ችግሮችን እየተጋፈጡ ቢሆንም የመነሻ፣ የመሻገሪያ እና የመድረሻ ሀገራት የብልጽግና፣ የፈጠራ እና የዘላቂ ልማት አቅም መሆናቸው የማይካድ እውነታ ነው ብለዋል።


 

በሐዋላ የሚልኩት ገንዘብ የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ከማቃናት ባለፈ የዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ሀገራትን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ረገድ ሚናው የላቀ መሆኑን ቅሰዋል።

የስደተኞች እውቀት፣ የልምድ ትስስርና ክህሎት ብርቱ እና ጽኑ ማህበረሰብን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በስደተኞች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ላሳደሩ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና መስጠቷን ጠቅሰው፥ ስደተኞችን በክብር መቀበል የማህበረሰብ ትስስርን እንደሚያጠናክር ማሳያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የፍልሰተኞች መዳረሻ እና መሻገሪያ መሆኗን ገልፀው፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ፣ ተገቢውን ከለላና ድጋፍ በማድረግ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ስምምነትን በተግባር እየፈጸመች ነው ብለዋል።

ስደተኞችን ከማስተናገድ ባለፈም ከተቀባይ ማህበረሰብ ጋር መልካም መስተጋብር እንዲፈጥሩ እያደረገች ያለው ጥረት በአርዓያነት የሚወሰድ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት ዜጋ ተኮር ፖሊሲን መሰረት በማድረግ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካና በሌሎች ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለሱን ጠቅሰዋል።

ዜጎችን ከመመለስ ባለፈ የሥነ-ልቦና ድጋፍ፣ የሕግ እገዛ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ መልሶ ማቋቋሚያ ዕድሎች እንዲመቻቹላቸው እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።


 

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ኢ-መደበኛ ስደት በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ላይ ከሚያስከትለው ከፍተኛ ጉዳት ባለፈ በሀገራት ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይዞ እንደሚመጣ አንስተዋል።

በስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ተወካይ አቢባቱ ዋኔ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች ለስደት እንደሚዳረጉ አንስተዋል።

ስደት የሰው ልጆች አስከፊ ታሪክን ብቻ ሳይሆን የጽናት ማሳያ፣ የተስፋ፣ የእድገትና የማህበረሰባዊ ትስስር መሰረት ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ስደቶችን በክብር ተቀብላ በማስተናገድ እያከናወነች ያለው አኩሪ ተግባር ለዓለም አርዓያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም