ቀጥታ፡

የብዝሃ-ሕይወት ሃብቶችን ለልማት ማዋል የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶች ተግባራዊ  እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የብዝሃ-ሕይወት ሃብቶችን ለልማት ማዋል የሚያስችሉ በርካታ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት የብዝሃ-ሕይወት ሃብቶች ወጥነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ሀገር አቀፍ የማህበረሰብ አቀፍ ዘር ባንክ ጥምረት በመመስረት ለባለድርሻ አካላት ይፋ አድርጓል።    


 

የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ (ዶ/ር) ፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ብዝሃ ሕይወት ኃብት ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የብዝሃ-ሕይወት የዘር አቅርቦትና መሠል ስራዎች ኢ-መደበኛና መደበኛ በሆነ መንገድ ይተገበሩ እንደነበር አስታውሰው፤ የዘር አቅርቦቱን ሳይንሳዊና ሙያዊ ለማድረግ የማህበረሰብ አቀፍ ዘር ባንኮች እንዲቋቋሙ መደረጉን አመልክተዋል። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሀምሳ ሶስት ማህበረሰብ አቀፍ ዘር ባንኮች መቋቋማቸውንም ነው የገለጹት።

የዘር ባንኮቹ በዋናነት የነባር ዘሮች ጥበቃ፣ የዘር አቅርቦትና ተደራሽነት እንዲሁም የምርምር ስራዎችን በማከናወን ለብዝሃ-ሕይወት ጥበቃ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል ነው ያሉት።

ኢኒስቲትዩቱ ሀገሪቱ ያላትን የብዝሃ-ሕይወት ሃብቶች ለልማት ማዋል የሚያስችሉ በርካታ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።


 

ከዚህ አኳያ የማህበረሰብ አቀፍ ዘር ባንኮች አቅምን ከፍ የሚያደርጉና የሚጠናከሩበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር አንዱና ዋነኛው መሆኑን አንስተዋል።

የጥምረቱ መመስረት ቀደም ሲል በተናጠል አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የማህበረሰብ አቀፍ ዘር ባንኮች በተናበበና ወጥነት ባለው መልኩ ጠንካራ የዘር ባንክ እንዲኖራት ያስችላል ብለዋል።

በኢኒስቲትዩቱ የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ ውብሸት ተሾመ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የማህበረሰብ አቀፍ የዘር ባንክ ጥምረት በሚመለከት የመሪነትና የአስተባባሪነት ሚና አለው። በዚህ ሒደት አጋር አካላት ድጋፋቸውን የሚያጠናክሩበት እድል ይመቻቻል ብለዋል።


 

ለዚህም ጥምረቱ የሚመራበት የአሰራር ስርዓት ለማበጀት የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ እንደተዘጋጀለትም አክለዋል።

ይህም የጥምረቱ አባል ማህበረሰብ አቀፍ ዘር ባንክነት ባሻገር መለስተኛ የብዝሃ ህይወት ማዕከል እንዲሆኑ እድል የሚፈጥር ስለመሆኑም መሪ ስራ አስፈጻሚው አብራርተዋል። 

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጥምረቱ በዘርፉ ወቅታዊነትን ያገናዘበና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህም ተቀራርቦ ለመስራትና ይበልጥ ምርታማ ለመሆን የሚያግዝ ሲሆን፤ ግልጽ አሰራር የተበጀለት መሆኑ ደግሞ ፍትሃዊነትን ከማስፈን አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

በተጨማሪም የብዝሃ ህይወት ሃብቶች በስፋት ያሉት በክልሎች በመሆኑ ጥምረቱ የክልሎችን ተሳትፎ በማጠናከር ረገድ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም