ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት አስደናቂ እድገት እያስመዘገበች ነው - የእስራኤል ምክትል አምባሳደር

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት አስደናቂ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ቶመር ባርሌቪ ገለጹ።

አምባሳደር ቶመር ባርሌቪ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ(POA) ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራች ለመሆን ያደረገችውን ጉዞ አድንቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው በስንዴ ራስን የመቻል ሀገራዊ ጉዞ ከፍተኛ ስኬት በማስመዝገብ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋትና ምርታማነትን በማሳደግ ያስመዘገበችው ሽግግር እንዳስደነቃቸው ጠቅሰዋል።

በተለይም ቀደም ሲል በየዓመቱ እስከ አንድ ቢሊየን ዶላር በማውጣት ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በማስቀረት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሏ ታሪካዊ ስኬት ነው ብለዋል።

መንግሥት ለስንዴ ምርት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ ትልቅ ለውጥ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የስንዴ አምራች እንድትሆን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።

እስራኤል በዘር ጥራት፣ በመስኖ ቴክኖሎጂ ወይም በአመራረት ዘዴዎች ያላትን ተሞክሮና የላቁ የግብርና ዘዴዎችን ልምድ እንደምታጋራ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ ለም መሬትና ከፍተኛ የሰው ኃይል ከቴክኖሎጂ ፈጠራ ጋር ሲቀናጅ አስደማሚ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ጠቁመዋል።

ምክትል አምባሳደሩ የኢትዮጵያ ስኬት ከሀገር አልፎ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ለማረጋገጥና የበለፀገች አህጉር ለመገንባት እንደ ምሳሌ የሚወሰድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም