የዲጂታል ገበያ ፕሮጀክቱ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያፋጥን ነው - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ገበያ ፕሮጀክቱ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያፋጥን ነው - ኢጋድ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ቀንድ የዲጂታል ገበያ ትስስር ፕሮጀክት ቀጣናዊ ትብብርን የማፋጠን አቅም ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ገለጸ።
ሁለተኛው የዲጂታል ገበያ ፕሮጀክት የስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ የየጀመረ ሲሆን የኢጋድ አባል ሀገራት፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የልማት አጋሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ተወካይ እና የተቋሙ የኢኮኖሚ እና ቀጣናዊ ትስስር ዳይሬክተር ሞሂ ቶሃሚ(ዶ/ር) የአፍሪካ ቀንድ የዲጂታል ገበያ ትስስር ፕሮጀክት ለቀጣናው መጻኢ ጊዜ መሰረት የሚጥል ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው ብለዋል።
የዲጂታል ንግድን አቅም ገልጦ በመጠቀምና የዲጂታል ስርዓቶችን በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
ፕሮጀክቱ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እና ከኢጋድ የቀጣናዊ ትስስር የረጅም ጊዜ ራዕይ ጋር የተጣጠመ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬታሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በስብሰባው የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም የሚገመገሙ ሲሆን በቀጣይ የትኩረት መስኮች እንዲሁም በፕሮጀክቱ ቀጣይ ምዕራፍ እና ለኢጋድ አባል ሀገራት አካታች ጠቀሜታዎችን ማስገኘት በሚችልባቸው ጉዳዮች ውይይት ይደረጋል።
ኢጋድ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ የተቀናጀ እና ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የዲጂታል ገበያን በመፍጠር በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን የማፋጠን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
እ.አ.አ 2023 የተጀመረው የአፍሪካ ቀንድ የዲጂታል ገበያ ትስስር ፕሮጀክት እስከ አሁን የዝግጅትና የሙከራ ምዕራፎችን አልፏል።
ከተያዘው 2025 አንስቶ እስከ 2027 ወደ ሙሉ ትግበራ እና ተደራሽነቱን ወደ ማስፋት ምዕራፍ እንደሚሸጋገርም ኢጋድ አስታውቋል።
በእ.አ.አ 2027 እና 2028 ዘላቂነት እና አካታችነትን ወደ ማረጋገጥ ምዕራፍ እንደሚሸጋገርም ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ቀንድ ዲጂታል ገበያ፣ የኢኮኖሚ ትስስር እና ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን ማጠናከርን ዋነኛ አላማው ያደረገ ነው።