ቀጥታ፡

በኢሉአባቦር እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ከማዕድን ልማት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

መቱ/አምቦ፤ታህሳስ 9/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የማዕድን ልማትን የማስፋትና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።

በሁለቱም ዞኖች በተያዘው በጀት ዓመት ለ12 ሺህ 749 ዜጎች በዘርፉ የስራ እድል መፈጠሩ ተገልጿል።

የኢሉአባቦር ዞን ማዕድን ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የማዕድን ሀብቶችን በአግባቡ በማልማት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።


 

ከእነዚህ ጥረቶች መካከል ዘርፉ በዋናነት የስራ እድል መፍጠሪያ እንዲሆን የማዕድን ሀብትን በመለየት ለልማት እንዲውል ማድረግ አንዱ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ህገ ወጥ  የማዕድን ማውጣት ስራዎችን መከላከል እንዲሁም ከማእድን ሀብት ግብይት ጋር የሚያያዙ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን የመግታት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ሕገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በተቀናጀ መልኩ በማከናወን የህግ ተጠያቂነት እየሰፈነ መሆኑን አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን በማዕድን ልማት ዘርፍ ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዞኑ በማዕድን ልማት ዘርፍ ተሰማርተው የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል አቶ አወል አህመድ፣ በግንባታ ድንጋይ ቁፋሮ መሰማራታቸውን በማንሳት በስራውም ተጠቃሚነታቸው እያደገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተሰማሩበት የስራ ዘርፍም  የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሌላው የዞኑ ነዋሪ አቶ አላሙዲን አባድር ከጓደኞቻቸው ጋር ተደራጅተው ለግንባታ የሚሆን ድንጋይ በማምረት በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸውን እየመሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የማዕድን ልማቱ ለዜጎችም ሆነ ለሀገር ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም መፍጠር የሚችል መሆኑን አንስተው በዘርፉ ሕገወጥነትን ለመከላከል እየተሰራ የሚገኘው ስራ  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አክለዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ሸዋ ዞን የማዕድን ልማትና ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ሽታዬ ቆሮ፤ በዞኑ የሚገኙ ማዕድን ሀብቶች እንዲለሙ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተለይም በዞኑ ለግንባታ የሚውሉ ድንጋይ እና አሸዋን ጨምሮ ሌሎች ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚያገለግሉ ጂፕሰም እና ላይምስቶን ጨምሮ ሌሎች ማዕድናትን በማልማት ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን አክለዋል።

ከእነዚህ የማዕድን ሀብቶች ልማት በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው በዘርፉ 8 ሺህ 749 ዜጎች በተለያዩ ማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከስራ እድል ተጠቃሚዎቹ መካከል የኤጀሪሳ ለፎ ወረዳ ነዋሪ አቶ በዳዳ ጉታ እንዳሉት፤ በዘርፉ ልማት በማህበር ተደራጅተው በመስራት ጥሩ ገቢ እያገኙ ነው።


 

ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ጌቱ ድሪባ፤ መንግስት ባመቻቸላቸው የብድር አቅርቦት ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በማዕድን ልማት እየተሳተፈ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም